Site icon ETHIO12.COM

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ያስተላለፉት መልዕክት

እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።

በአሁኑ ሠዓት አሸባሪው የትህነግ ቡድን በክልላችን አንዳንድ የከተማም ሆነ የገጠር አካባቢዎች በርካታ ሰርጎገቦችን ለማሰማራት እና ሀሰተኛ መረጃን በማኅበረሰቡ ውስጥ በመንዛት ህዝባችንን ለማወናበድ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው የንግድ፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ እና በአብያተ እምነቶች ጭምር ተሰራጭተው ህልውናችንን ለማስከበር በገባንበት ጦርነት ዙሪያ ውዥንብር የመፍጠር እቅድ ላይ መጠመዳቸውን ተገንዝበናል፡፡

እነዚህ የጥፋት መልእክተኞች ለሀገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል በሚረጩት መርዛማና ሀሰተኛ ወሬዎች ህዝብን በማሳሳት ኅብረተሰቡ በራሱ የጸጥታ ኃይሎችና በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ የማድረግ ተልዕኮ የተሠጣቸው ስለመሆኑ የባንዳ ድርጊቶቻቸው ያስረዳሉ፡፡

“መንግሥት ለወያኔ አሳልፎ ሊሰጠን ነው፤ የጠላት ኃይል አይሏል፤ ሠራዊቱ ጥሎን እየሸሸ እና እየተበተነ ባለበት ሰዓት እኛ ለምን እንዘምታለን? እዚሁ ሆነን የሚሆነውን እናያለን፤ ለዚህ ሁሉ ያበቃን የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል መንግስት ነው፤ ከካዱን መሪዎች ጋር እንዴት ብለን አብረን ሆነን ልንዋጋ እንችላለን?” የሚሉ እና የመሳሰሉትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በመንዛት ህልውናውን ለማስጠበቅ በተጋድሎ ላይ የሚገኘውን ህዝብ ሥነ ልቦና ለመሥለብ እየተንፈራገጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ ድርጊታቸው ህዝብ አንድ ሁኖ በአሸባሪው ትህነግ ላይ የጀመረውን ዘመቻ እንዳይቀጥል እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ እና መንግሥት የሀገር እና የህዝብን ህልውና ለማስጠበቅ የሚተገብራቸውን አቅጣጫዎች ተቀብሎ እንዳይተገብር የማነሳሳት ዓላማን ያነገበ ነው፡፡

በተጨማሪም በውስጣችን የሚገኙ አንዳንድ ሆድ አደር ግለሰቦችን በገንዘብ በመደለል ህዝባችን አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ የሚያደርጋቸውን የሥልጠና፣ የሥንቅ ዝግጅት፣ የጦር አደረጃጀት፣ ሥምሪት እና ወታደራዊ የቦታ አሰፋፈርን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ተቀብሎ ለጠላት ኃይል በማሻገር በወገናችን የሰው ኃይል፣ ቁሳዊና የሥነ ልቦና እንዲሁም በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ሌላኛው የጥፋት ተልእኳቸው አካል ነው፡፡

ሰርጎ ገቦቹ የስለላ እና የብተና ተልዕኳቸውን ለማስፈፀም ነጋዴ፣ ጎዳና ተዳዳሪ፣ ህጻናትና አዛውንት፣ የሀይማኖት መሪ፣ የአእምሮ ህመምተኛ፣ በልመና ተዳዳሪ፣ የመስተንግዶ ሰራተኛ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ በመምሰል በፀጥታ ተቋሞቻችን ጭምር ሰርጎ ለመግባት የሚያደርጉትን ስርሰራ ነቅቶ መጠበቅ እና ተግቶ መልቀም ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል የግድም ይላል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ወገኖች የገባንበት ጦርነትን ነባራዊ ሁኔታ ሙሉ ገጽታውን ሳይረዱ አንዱ ሌላውን በማኅበራዊ ሚዲያ በመዝለፍና ያልተገባ መረጃን ለጠላት በሚያመች መልኩ በፌስ ቡክ በማሰራጨት የራሳቸውን ህልውና በተጻረረ መልኩ በራሳቸው ላይ ሲዘምቱ ተስተውለዋል፡፡

ከፊሎቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያን ይህን መሰሉን ራስን የመብላት ድርጊት የሚፈፅሙት ከጠላት ኃይል ለሚያገኙት መናኛ ዲናር ሲሉ መሆኑ ቢታወቅም አብዛኞቹ ግን ይህን መሰሉ ድርጊት የሚከውኑት የሀገር እና የራሳቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ፋይዳ ይኖረዋል ከሚል እሳቤ ተነስተው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

ይሁን እንጂ የወገንን ሚሥጥር ለጠላት ኃይል በፌስ ቡክ በይፋ መንዛትም ሆነ የአሸባሪው ትህነግ የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎችን ተቀብሎ ማራገብ ለሀገርም ሆነ ለህዝብ ህልውና ሥለማይጠቅም ከዚህ መሰሉ ድርጊት ፈጥኖ ራስን ማረም እና የማይታረሙትን ጥቆማ በመስጠት የ”እሾህን በእሾህ” ሥልት ልንከተል ይገባል፡፡

በሁላችንም ህልውና ላይ ያነጣጠረውን የመጥፋት አደጋ ለመመከትም ሆነ ለመቀልበስ የሁላችንም ሚና ያስፈልጋል። አንድነታችንን አስጠብቀን እስከቆምን ድረስ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በህልውናችን ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ እኛ ከበቂ በላይ ሁለንተናዊ ኃይል አለን፡፡

ከአንድነታችን የመነጨው ኃይላችን የትህነግን ታጣቂዎችንም ሆነ ሰርጎ ገቦችን በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ግዜ ትቢያ የማድረግ አቅም እንዳለው ቅራቅር ምስክር ናት፡፡ አንድነታችን ይዘን መቆም የጀመርን እለት ራሳችንን ከመከላከል አልፈን በአሸባሪው የትህነግ አንጋቾች የጥቃት ከበባ ውስጥ ወድቆ የነበረ የወገን ኃይልን ከሞት ላንቃ ፈልቅቆ የማውጣት ምትሃታዊ ገድል የፈጸምን ህዝቦች መሆናችንን ወዳጅም ጠላትም አይዘነጋውም።

እንደ ትላንትናው ሁሉ ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም ውስጣዊ አንድነታችንን እናስቀጥል። አስተማማኙ ጋሻችን አንድነታችን ብቻ ነው። አንድነታችንን ለማላላት ዓልሞ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዛ ሰርጎ ገብ በጦር ሜዳ ምላጭ ከሳበብን ጠላት የበለጠ የህልውናችን ጠንቅ ነው፡፡

ስለሆነም ህልውናችንን ለማስቀጠል በጦር ግንባር ከምናደርገው ተጋድሎ ባልተናነሰ መልኩ በዙሪያችን የሚርመሰመሱ ሰርጎ ገቦችን የመለየት፣ የመመንጠርና የመልቀም ሥራ የሁላችንም የቤት ሥራ ነው!!!

በተረፈ አሸባሪውን ትህነግ የመምታት ስራ በተጠና መንገድ እየቀጠለ ድል እያስመዘገበ ነው። ዝርዝር መረጃውን በቀጣይ ቀናት የምናደርሳችሁ ቢሆንም አሁን ላይ በሁሉም አውደ ውጊያዎች የተሰለፈው የወዳጅ ወገን ያለ እረፍት ተልኮውን እየተወጣ ነው።
ድል ለአማራ !!
ድል ለኢትዮጵያ!!!

Exit mobile version