Site icon ETHIO12.COM

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በጀመረችው የህልውና ክተት ጥሪ ላይ ዘመቻ ከፈቱ

fact check

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱት ያለውን አፍራሽ ዘመቻ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ኮነነ፤

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከአሸባሪው ህዋሓት ጥቃት እንዲከላከሉ እና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ትላንት ያቀረበውን ጥሪ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አዛብተው በተሳሳት ሁኔታ እያሰራጩ መሆናቸውን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል፡፡

መንግስት ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ያስተላለፈውን አገርን ከአሸባሪው ህወሓት ቡድን የመታደግ ጥሪ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አውነታውን በማዛባት በኢትዮጵያ ላይ አፍራሽ ዘመቻ በማድረግ ላይ ናቸው ብሏል፡፡

ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ፋይናንሺል ታይምስ፤ ዎል ስትሪት ጆርናል፤ሮይተርስ እና አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የትላንቱን የመንግስት መግለጫ ጭብጥ በማንሻፈፍ ለተደራሲዎቻቸው ማድረሳቸውን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያው አመልክቷል ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያና ጥቃት ሲያደርስ መገናኛ ብዙኃኑ አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ አልፈው ትላንት መንግስት ለህዝቡ ያስላተለፈውን ሀገርን የማዳን ጥሪ በማዛባት ትግራይን ለማጥቃት የተደረገ ጥሪ አድርገው ማቅረባቸውን በመኮነን የሽብር ቡድኑ የታወጀው ዘመቻ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚያገናኘው አለመኖሩን ገልጿል፡፡

እነዚሁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አሸባሪው ህወኃት በንፁሃን ሰዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በዜናዎቻቸው ከማንሳት ይልቅ ችግሩን በመንግስት ሲያላክኩ ታይቷልም ብሏል፡፡

አሸባሪው ቡድን ሰላምና መረጋጋት የራቃት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር እየሰራ ያለውን አፍራሽ ድርጊት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃኑ በዜናዎቻቸውም ሆነ በአርስቶቻቸው ምንም አለማለታቸውን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያው ተችቶታል፡፡

በኢትዮጵያ ህጋዊ ስርዓትን ተከትሎ በአሸባሪነት የተፈረጀውን ቡድን አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃኑ ለመቀበል እያንገራገሩ መሆኑ በተለይም ዋሽንግተን ፖስት እና ፣ አሶሼትድ ፕሬስ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን መሰረታዊ ስነ ምግባር ነፃነት በመተው በግልፅ ለአሸባሪ ቡድን አጋርነት በማሳየት ላይ ይገኛሉ ሲል ወቅሷል፡፡

እንደ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ መንግስት ላለፉት ጥቂት ሳምንታት የመከላከያ ኃይሉን ከትግራይ እንዲወጣ በማድረግ የአካባቢው ማህብረሰብ የክረምት እርሻውን ነፃ ሁኖ እንዲያርስ እና የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ እንደነበር አስታውሷል፡፡

ይሁን እንጂ የታወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት በመጣስ በአገራባች ክልሎች ላይ ወረራ በመፈፀም በንፁሃን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ እየሰፋ በመምጣቱ እና መሰረተ ልማቶችን ማውደሙ በመቀጠሉ መንግስት በትላንተናው ዕለት የተናጠል ተኩስ አቁሙን በማንሳት የፀጥታ ኃይሎች በተባበረ ክንድ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ መተላለፉ ተመልክቷል።


Exit mobile version