Site icon ETHIO12.COM

“ራዕይ ለተጋሩ” ኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ ተመሰረተ – “አደዋ የተፈለፈሉ” ጥቂት የስልጣን ጥመኞች ተውገዙ

በትግራይ ተወላጆች አማካኝነት ራዕይ ለተጋሩ ኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ ተመሰረተ።የህዝባዊ ንቅናቄውን ምስረታ በማስመልከት በዛሬው እለት አስተባባሪዎቹ መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ ሊላይ ሃይለማርያም በመግለጫው ላይ እንደገለጹት፤ በተወሰኑ የአድዋ ሰዎች የትግራይ ህዝብ እየተበደለ ይገኛል።

“የትግራይ ህዝብ ላለፉት ሶስት ሺህ አመታት ለሀገረ መንግስት ግንባታ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር የራሱን አሻራ ያስቀመጠ ህዝብ ነው” ያሉት አቶ ሊላይ፤ በአሁኑ ወቅት ከአድዋ በተፈለፈሉ ትግራይን ለመገንጠል አስበው ሳይሳካላቸው በቀሩ ለህዝብ በማይጠቅሙ ቡድኖች መጠቀሚያ ሊሆን አይገባም ብለዋል።

አቶ ሊላይ በመግለጫው እንዳስታወቁት፣ የንቅናቄው አላማም እነዚህ የትግራይን ህዝብ በተሳሳተ መንገድ ባይተዋር እንዲሆን እየሰሩ ያሉ ሀይሎችን ለመመክት ያለመ ነው። ሰለሆነም በአሁኑ ሰዓት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት የአንድ ቡድን እኩይ አላማን ለማሳካት መሆኑን አውቆ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የትግራይ ህዝብ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል ብለዋል።

ህወሃት በትግራይ ህዝብ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለው በደል አድርሷል ያሉት አቶ ሊላይ፤ አሁንም ለ27 አመት የሰራው በደል አልበቃው ብሎ ህዝቡን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። ንቅናቄው በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ተጋሩን በማደራጀት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ህዝባዊ ንቅናቄው 7 ምሶሶዎች ያሉት ሲሆን 5 ምሶሶዎች ከቀዳማይ ወያነ የተወሰዱ ናቸው ብለዋል።

ንቅናቄው የማንም ፖለቲካ ድርጅት ውግንና የሌለው መሆኑ የገለፁት የንቅናቄው አመራር አባል አቶ አታኽልቲ ሃይለስላሴ፤ የንቅናቄው አበይት አላማዎችም፤

1.ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉ ተጋሩ ጥቂቶች እና የትግራይን ህዝብ የማይወክሉ ናቸው። የትግራይን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡም ልክ አለመሆናቸው እና የትግራይ ህዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ሃገሩን እንዲያፀና ይሰራል፤

2. በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ተጋሩ ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ጋር እንሰራለን፤

3. ጦርነት ሃገር ነው፤ የትግራይ ወጣት ለጥቂት የስልጣን ጥመኞች ብሎ መስዋእት መክፈል እንደሌለበት ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል። በየትኛውም ቦታ ያለ ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ በዚህ ንቅናቄ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል

በሞገስ ተስፋ – ኢፕድ

Exit mobile version