Site icon ETHIO12.COM

“…የማይተኩስ ነገር ግን ወደ ጠላት ምሽግ ሰተት ብሎ ለመግባት የሚሞክር ተዋጊ” የትህነግ “ስልጡን” የውጊያ ስልት

በሕግ ማስከበር ዘመቻው የነበረውን አንጸባራቂ ድል በሕልውና ዘመቻው ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን የአማራ ልዩ ኀይል አዛዦች ገለጹ፡፡የአማራ ልዩ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊትና ከሚሊሻ አባላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በሕግ ማስከበር ዘመቻው አሸባሪው ትህነግን ድባቅ በመምታት ሀገርን በልዩ ወታደራዊ ብቃት ታድጓል፡፡ ከወታደራዊ ሳይንስ ልህቀታቸው በተጨማሪ ወታደራዊ ዲሲፕሊናቸው ያፈራቸውን ማኅበረሰብም ይመስላሉ፡፡ ኩሩ፣ ደፋር እና ትሁት ስለመሆናቸው ለስዓታት አብሯቸው የተቀመጠ ሁሉ መመስከር ይችላል፡፡

በነሐሴ ክረምት ሙቀቱ አብዝቶ በሚፈታተንበት የተከዜ ወንዝ ዳርቻ ለአማራ ሕዝብ ዘላለማዊ ነፃነት ራሳቸውን እንደ ሻማ እያቀለጡ የድል ጮራን ያበራሉ፡፡ አሁን ደግሞ ብቻቸውን አይደሉም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው የኢትዮጵያን ሕልውና ለመታደግ ከአራቱም አቅጣጫ የመጡት የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት እና የመከላከያ ሠራዊቱ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ ሆነዋል፡፡

ሻምበል ደሳለኝ አምባው የተከዜ ወንዝን ተከትሎ እንደንብ ከሰፈረው የአማራ ልዩ ኀይል መካከል የአንድ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ናቸው፡፡ ረጅም ዘመናቸውን በውትድርና ሙያ እንዳሳለፉ የሚናገሩት ሻምበል ደሳለኝ “ገንጣይ አስገንጣይ ወንበዴ” የሚሏቸው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን አባላት ከመንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በኋላ በዚህ አካባቢ 11 ጊዜ ጦርነት መክፈታቸውን ነግረውናል፡፡

“አሸባሪው ቡድን በውትድርና ሕይዎቴ አንድም ቀን አይቸው የማላውቀው አይነት ጦርነት ሲከፍት አስተውያለሁ” የሚሉት ሻምበል ደሳለኝ ስምሪታቸው ከወታደራዊ ሳይንስ እና ስልት ውጭ ግብዝነት የተሞላበት ነበር ይላሉ፡፡ ምክትል አዛዡ እንደሚሉት እስካሁን በተደረጉት ውጊያዎች የተረዱት ነገር ቢኖር አሸባሪው ትህነግ ለጦርነት የሚልካቸው ቡድኖች ምንም አይነት የመሰረታዊ ውትድርና እውቀት እንደሌላቸው ነው፤ አይደለም ወደ ጦርነት መሰማራት ጦርነት በሚደረግበት አካባቢ መኖር የማይገባቸው ሕጻናት የጦርነቱ ፊታውራሪ ሆነው ሲመጡ እንደማየት አሳዛኝ ድርጊት አይኖርም ነው ያሉት ሻምበል ደሳለኝ፡፡

በሁመራ ግንባር ከተሰማራው የአማራ ልዩ ኀይል የአንድ ሻምበል ምክትል አዛዥ የሆኑት ዋና ሳጅን ግርማ በላይ እስካሁን በተደረገው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ተደጋጋሚ ጦርነት ተከዜን መሻገር የቻለ የለም ብለዋል፡፡

በአካባቢው በተደረገው ጦርነት አሸባሪው ትህነግ የተዋጋው በወታደራዊ ሳይንስ በተካነ መንገድ ሳይሆን ሃሽሽ ስንቁ እና ትጥቁ ባደረገ ቡድን መሆኑንም ነግረውናል፡፡ “በየትኛውም ዓለም በተደረገ ጦርነት የማይተኩስ ነገር ግን ወደ ጠላት ምሽግ ሰተት ብሎ ለመግባት የሚሞክር ተዋጊ አልተሰማም” የሚሉት ዋና ሳጅን ግርማ ሕጻናትን በሃሽሽ አደንዝዞ መላክ የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው ይላሉ፡፡

ተከዜን መሻገር የአሸባሪው ቡድን የቀን ቅዥት ነው የሚሉት አዛዦቹ በአካባቢው የተሰማራው የአማራ ልዩ ኀይል እና የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያሳየውን የላቀ ግዳጅ አፈጻጸም በሕልውና ዘመቻው ለመድገም መዘጋጀቱንም ነግረውናል፡፡ ሕዝቡ ለሠራዊቱ ደጀን መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን የገለጹት የልዩ ኀይል መሪዎቹ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከሁመራ ግንባር አሚኮ

Exit mobile version