Site icon ETHIO12.COM

ከሱዳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሾልኮ የገባ የሽብር ሃይል ተደመሰሰ

በሱዳን በኩል ሾልከው ወደ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አልመሃል አካባቢ በመግባት ሽብር ለመፍጠር እና በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረሰ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ ከ170 በላይ የሚሆኑት መደምሰሳቸውን የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በክልሉ እና ከክልሉ ወጪ ከሚንቀሳቀሱ ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመፍጠር ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በእነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ መወሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ አካላት እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙት የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት ጋር በመቀናጀት እስከትናንት በተወሰደው የሕግ የማስከበር እርምጃ ከ170 በላይ የሚሆኑ ጸረ ሰላም ኃይሎች ተደምስሰዋል ብለዋል፡፡

የተደመሰሱት ጸረ ሰላም ኃይሎች በሱዳን ድንበር በኩል በመግባት በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው ጉባ ወረዳ አልመሃል ቀበሌን እንደ ማዕከል ተጠቅመው ወደ ግድቡ የሚወስደውን መስመር በመቁረጥና እንቅስቃሴን በማወክ ሥራውን ለማስተጓጎል ዓላማ የነበራቸው መሆኑን አቶ አብዮት ገልጸዋል፡፡ ጸረ ሰላም ኃይሎቹ የህዳሴ ግድብ ሥራውን ከማስተጓጎል ባለፈ በክልሉ ሽብር በመፍጠር በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የማድረስ ዓላማ እንደነበራቸው እና አልማሃልን ማዕከል በማድረግ ወደ አማራ ክልል ለመንቀሳቀስ ዕቅድ እንደነበራቸውም የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዮት አልቦሮ አስረድተዋል፡፡

በተወሰደው እርምጃ ከተደመሰሱት ጸረ ሰላም ኃይሎች መካከል ከ16 በላይ የሚሆኑት የአሸባሪው ሕወሓት አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃም ወደ አካባቢው በገባው የጠላት ኃይል ላይ ከባድ ኪሳራ ማድረስ ተችሏል ያሉት አቶ አብዮት ከተደመሰሱት በተጨማሪ አብረው የገቡ በርካታ የአሸባሪው ሕወሓት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች መቁሰላቸውንና መማረካቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በቀጣይም በሁሉም አካባቢዎች በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ የጀመረውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። የክልሉ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች በተደራጀ መልኩ በማንኛውም ቦታ በጸረ ሰላም ኃይሉ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን እንዲደግፉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃን ጠቅሶ ኢብኮ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version