ETHIO12.COM

በጋምቤላ ከተማ በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ተላላኪነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በጋምቤላ ከተማ በአሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ተላላኪነት የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችን ከጦር መሳሪያና ሌሎች ቁሳቀሶች ጋር በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ሁለቱ የቀድሞን የሀገር መከላከያ የደንብ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የህክምናና ሌሎች ቁሳቁሶችን ይዘው ከጋምቤላ ከተማ ወደ ጫካ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ነው።

ቀሪው ተጠርጣሪ ደግሞ ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ በቤቱ በተደረገ ፍተሻ አንድ ዘመናዊ የጦር ሜዳ መነጽርና አንድ ሽጉጥ ተገኝቶበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ተጠርጣሪው ካሁን በፊትም ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳለው ተጠርጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ እየተደረገ ያለው ተጨማሪ ምርመራ ሲጠናቀቅ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት እንደሚላክ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ክልሉ ጠረፋማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህወሃትና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች ሰረገው እንዳይገቡ የክልሉና ፌዴራል የጸጥታ አካላት የቁጥጥር ስራ እያካሄዱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅና የአሸባሪ ቡድኖች ተላለኪዎችን አጋልጦ በመስጠት ረገድ የጀመረው ተሳተፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Exit mobile version