Site icon ETHIO12.COM

በማይጠብሪ ግንባር በጠላት ላይ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ – ስትራቴጂክ ቦታዎችን ለቀቀ

የ24ኛ ቴዎድሮስ ክፍለ ጦር በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡

በዚህም ጦሩ በማይጠብሪ ግንባር በጠላት ላይ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን አስታውቋል፡፡

ክፍለ ጦሩ የተለያዩ መሣሪያዎችን ማርኳል ፥ በአሁኑ ጊዜም የተበታተነውን የአሸባሪውን ቡድን አባላት በማደን እየደመሰሰ መሆኑን አመላክቷል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኀይል በማይጠብሪ ግንባር ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ ነው፦ ኮሎኔል የሺበር አዳነ

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኀይል በማይጠብሪ ግንባር ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የ54ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል የሺበር አዳነ ተናገሩ።

በማይጠብሪ ግንባር ለዳግም ወረራ የተነሳው አሸባሪውና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እየተደመሰሰ መሆኑን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን በግንባር ተገኝቶ ተመልክቷል።

በማይጠብሪ ግንባር ያነጋገርናቸው የ54ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል የሺበር አዳነ እንደገለጹት ሽብርተኛው ትህነግ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጠላትን ለማሸነፍ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ መግባቱ እየተመዘገበ ላለው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ኮሎኔል የሺበር አስታውቀዋል።

ኮሎኔሉ ሽብርተኛው ትህነግ ከዓመታት በፊት የቀየሰውን የጦርነት ስልት እየተከተለ መሆኑን ነው የተናገሩት። ዋና አዛዡ አሸባሪው ቡድን በአሁኑ ወቅት ጦርነቱን በመሣሪያ ሳይሆን በሰው ማዕበል ለመምራት ጥረት እያደረገ ነው፤ አቅሙም እየተዳከመ መጥቷል፤ የትግራይ ወላጆችም ልጆቻቸው የእሳት ራት ከመሆናቸው በፊት ሊታደጓቸው ይገባልም ብለዋል።

ሠራዊቱ ሰንሰለታማ ተራሮችን ተጋፍቶ እያሸነፈ የመገስገሱ ምስጢርም ሕዝባዊ ደጀን በመኖሩ ነው ብለዋል። ሕዝቡም በቅርቡ ወደ ተረጋጋ ሰላም ይመለሳል ነው ያሉት የ54ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል የሺበር ሲል አሚኮ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ስትራቴጂክ ቦታዎች አስለቀቀ

አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ትንኮሳ ያደረገባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ማስለቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ቆቦ ከተማን በመቆጣጠር ወደ ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በቀላሉ ለማለፍ በተለምዶ የአርሴማ ተራሮች የተባሉ አራት ተራሮችን ተቆጣጥሮ ለቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ነበር።

ሆኖም የፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አነስተኛ የሰው ሃይልና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ብቻ በመጠቀም በርካታ የጁንታውን ሃይል በመደምሰስ አራቱንም ተራሮች በአንድ ቀን በማስለቀቅ ለአካባቢው ሚሊሺያ ማስረከብ መቻላቸው ተገልጿል፡፡

የሰሜን ዳይሬክቶሬት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢ/ር ሀሰን አብዱ፤ የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አሸባሪውን የህወሓት ጁንታ ቡድን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፣ የተማመነባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች አስለቅቋል፡፡

የአሸባሪውን ታጣቂዎች በመደምሰስ ለአካባቢው ማህበረሰብ መረጋጋትን ፈጥረዋል፡፡

አባላቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌላ ግዳጅ ለመሰማራት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ትእዛዝ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል። (ኢዜአ)

Exit mobile version