Site icon ETHIO12.COM

አማራ ክልል አጋጣሚ ተጠቅመው ጥቅም በሚያግበሰበሱ “ከሃዲዎችንና ሽብር የሚነዙ” ያላቸውን “በቃ”አለ

“የትኛውንም ሽብር መንዛትና አሻጥር አንታገስም!” የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

ለሕዝባችን ደህንነት መረጋገጥ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን!!

አሸባሪውና ወረሪው ትህነግ በክልላችን ላይ እንደ ሕዝብ ጥቃት ከፍቶብናል፡፡ በወረራቸውና ገብቶ በወጣባቸው አካባቢዎች ከሚፈጽማቸው ጭፍጨፋዎች ጎን ለጎን በአይነቱ የተለየ የንብረት ዘረፋና ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡ የዚህ የጥፋት ዓላማ ተጋሪዎች ጦርነቱን ዘርፈ ብዙ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ በክትትል መረጃችን ቀድመን ደርሰንበታል። እርምጃዎችን በመውሰድ ላይም እንገኛለን፡፡ የወራሪውና የሽብር ቡድኑ ቅርንጫፎች እንዲሁም አጋጣሚውን ተጠቅመው ሀብት ማጋበስ የሚፈልጉ ከሃዲዎች በአንዳንድ አካባቢዎች በመታየት ላይ ናቸው፡፡

ከወረራው ባሻገር በየአቅጣጫው ያለው ሕዝባችን ላይ ሌሎች ጉዳትና ጫናዎችን ለማድረስ የሚጥሩ አሻጥረኞች ከአሸባሪው ትህነግ ለይተን አናያቸውም።

በመሆኑም፡-

1ኛ .በአንዳንድ ከተሞቻችን ሆን ተብሎ የመሰረታዊ ፍጆታና ሸቀጣሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ ሕዝብን ለማማረር የሚሰሩ አንዳንድ የንግዱ ዘርፍ አባላት አሉ፡፡ በርካታ የንግዱ ማኀበረሰብ አባላት በቻሉት መጠን የሕልውና ዘመቻውን በመደገፍ ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ ባሉበት ወቅት፣ ከዚህ በተለየ አፍራሽና ጸረ-ሕዝብ በሆነ መንገድ የዋጋ ንረቱን እንዲያሻቅብ እያደረጉ ያሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡

በዚህ የሕልውና ዘመቻ አርሶ አደራችን ማሳውን ትቶ፣ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ገበታቸው ተነስተው፣ የመንግሥት ሠራተኛው ከወርሃዊ ደመወዙ መዋጮ በማዋጣት ሕዝብን ከጠላት ለመከላከል ርብርብ በሚደርጉበት ታሪካዊ ወቅት አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ነጋዴዎች ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የዋጋ ንረት ሲፈጥሩ መታየታቸው፣ ድርጊቱ በውጤት ደረጃ ጠላትን የሚጠቅም ሕዝባችንን ለጫና የሚዳርግ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል፡፡

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው በየደረጃው ከሚገኙ የንግድ ቢሮ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራንበት ቢሆንም በዚህ መሰል ድርጊት የሚሳተፉ የንግዱ ማኀበረሰብ አባላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እናሳስባለን፡፡

2ኛ.የሕልውና ትግሉን ጊዜ ተጠቅመው በሕገ-ወጥ ንግድ በመሰማራት ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን በማስወደድ ሕዝባችን ላይ ሌላ የጦርነት ግንባር በመክፈት ላይ የሚገኙ አካላት እንዳሉ ይታወቃል። በዚህኛው ሕገ-ወጥ የንግድ መስክ ተዋናይ የሆኑ አብዛኛዎቹ አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከቀደሙ ክትትሎችና ሪከርዶች መረዳት ይቻላል፡፡ መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራትን ከፖለቲካ ዓላማ አኳያ የኢኮኖሚ ድቀት ለመፍጠር አልመው የሚሰሩ በመሆኑ ክትትላችን በማጠናከር ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንቀጥላለን፡፡ በዚህ ተግባር የሚሳተፉ ሕገ-ወጦች ድርጊታቸውን ከተከፈተብን ጦርነት ለይተን እንደማናየው መታወቅ አለበት።

3ኛ.በሕዝባችን ላይ ሐሰተኛ መረጃዎችንና አሉባለታዎች በማሰራጨት ላይ የሥነ ልቦና ጫና ለማድረስ የሚሰሩ፣ በሕልውና ዘመቻው የተሳተፉ አካላትን ትኩረት ለመበተን ሆን ተብሎ የጠላት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላት ከጠላትና ሰርጎ ገቦች ለይተን አናያቸውም፡፡ የፀጥታ ኃይላችን በሐሰተኛ መረጃዎች ዙሪያ የጠላትን ሴራና አሻጥር እያስፈፀሙ ያሉ አካላትን በጥብቅ እየተከታተለ የሚገኝ ሲሆን፤ ሕዝባችን በመሰል የጠላት መስመር የተሰለፉ አካላትን በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

4ኛ.በአንዳንድ የክልላችን ከተሞች ሰላምና መረጋጋት የሚያደረፈርሱ ድርጊቶች አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ፡፡ ሰበብ እየፈጠሩ ጥይት ወደላይ መተኮስ የነዋሪውን ሠላምና መረጋጋት ሲፈትን ይስተዋላል፡፡

በመሆኑም በየትኛውም የክልላችን ክፍል ወደ ጠላት እንጅ በሰበብ አስባቡ ወደላይ የሚተኮስ ጥይት ሊኖር አይገባልም፡፡ ካለም ሕግ መተላለፍ ብቻ ሳይሆን ካለንበት የሕልውና ትግል አኳያ የጠላት አጋዥ የመሆን ያህል ወንጀል ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም ሕገ-ወጥ ተኩስ በሚተኩስ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ላይ የሕግ የበላይነትን እናስከብራለን፡፡

5ኛ.ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የምሽት ትራንስፖርት ስምሪት ምደባና የሰዓት ገደብ በተጣለባቸው ከተሞችና ወረዳዎች፣ ለሕዝባችን ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ሲባል ተፈጻሚነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በልዩ ሁኔታ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ፍቃድ ከተሰጣቸውና የስምሪት ፍቃድ ካላቸው ውጭ ሲንቀሳቀሱ የሚገኙ የትኞቹም ተሸከርካሪዎች በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

6ኛ.እንደ ሀገር እና እንደ ክልል በተጠናከረ ሁኔታ የጀመርነውን የሕልውና ዘመቻ ለመቀልበስ ጠላት የተለያዩ ሰርጎ ገቦችን ለመጠቀም በመሞከር ላይ ነው፡፡ በእስካሁኑ ክትትላችን በሕዝባችን ጥቆማ በርካታ ሰርጎ ገቦችን በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ ሰርጎ ገቦች መምጫቸውና ማረፊያቸው ዓይነተ-ብዙ በመሆኑ፣ በሆቴሎች የሚስተናገዱ እንግዶች ማንነትና የቆይታ ሁኔታ፣ የቤት አከራዮች የአዳዲስ ተከራዮቻቸውን ማንነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማድረግ አንዳተጠበቀ ሆኖ፣ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማችሁ ለጸጥታ አካላት በፍጥነት ሪፖርት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን አለማድረግ በሕግ ያስጠይቃል፡፡

የህልውና ትግላችን ግብ እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር የገጠመንን ጠላት በማሸነፍ የአማራንና የኢትዮጵያን ህልውና በአስተማማኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም ጠላትን ከመታገል ጎን ለጎን የትኛውንም ሽብር የመንዛትና አሻጥር አንታገስም! ለሕዝባችን ደኅንነት መረጋገጥ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን!!

የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም.

Exit mobile version