Site icon ETHIO12.COM

❝ሰርጎ ገቦችን የማጋለጡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል❞ የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

አሸባሪው ትህነግ በሰርጎ ገቦች በኩል ሕዝብን ለመረበሽ የሚያደርገውን ጥረት ሕዝብና የጸጥታ ኀይላችን በትብብር እየሠሩበት ይገኛል። አሸባሪው ትህነግ ሰርጎ ገቦቹን ሕዝብ የሚወደውን፣ የሚታዘንላቸው፣ ኀላፊነት ያላቸው፣ የሐሰት ማንነት በማላበስ በሕዝባችን ውስጥ ሰርጎ ለመግባት ጥረት ለማድረግ ሲሞክር በተደጋጋሚ ተጋልጧል። አሁንም በተለያዩ አደረጃጀቶች፣ በማኅበረሰብና ተቋማት ውስጥ አልፎም በጦር ግንባር አካባቢ የሰርጎገብ ሽብር ሙከራዎች እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች አሉን። ስለሆነም፡-

1) የጸጥታ ኃይሉና ሕዝባችን በፍተሻ ቦታዎች ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥሩን ከወትሮው በጠነከረ መንገድ እንዲፈፅም እናሳስባለን። በየአካባቢው በሕዝብ የሚጠበቁ ኬላዎችም ያለመታከት ቁጥጥር እንዲያደርጉ በተለይም በዝናብ ወቅት፣ ሌሊት በአጠቃላይ ጠላት ቁጥጥር ይቀንሳል በሚልባቸው ጊዜያቶችና በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት።

2) ተመሳስለው የሚሠሩ ሰርጎ ገቦችም ሆነ ጸጉረ ልውጦች ሲገኙ ወጣቱ ለጸጥታ ኀይሉ ጥቆማ ከማድረግ፣ ይዞ ለጸጥታ ኀይል ከማስረከብ ውጭ ያልተገባ ድርጊት ውስጥ መግባት እንደሌለበት እናሳስባለን። አሸባሪው ኃይል አንደኛው ስልቱ ሕዝብ ውስጥ ትርምስና ቅሬታ መፍጠር በመሆኑ ለሕዝባችን ይጠቅማል ብለን የምናከናውነው ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በወጣቱ ውስጥ ሠርጎ በመግባት ስህተቶች እንዲሠሩ ማድረግ አንዱ የጠላት ዓላማ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ግላዊ ፍላጎቶች ያላቸው አካላትም ቢሆን አጋጣሚውን የመጠቀም አዝማሚያ ስለሚኖር ሰርጎ ገብና ጸጉረ ልውጦች በሚገኙበት ወቅት በሕጋዊ አግባብ ለጸጥታ ኀይሉ መጠቆም ወይንም ይዞ መስጠት ያስፈልጋል።

3) የምሽት የጊዜ ገደብ በተጣለባቸው ከተሞች ሕጉን በማክበርና ከሰዓት ገደብ በኋላ ባለመንቀሳቀስ የጸጥታ ኀይሉንና በበጎ ፈቃደኝነት ግዳጅ የተሰጣቸውን ወጣቶች በመተባበር ለአካባቢያችን ጸጥታ የበኩላችንን ማድረግ ያስፈልጋል። ሰርጎ ገቡ ኃይል እንዲህ ያሉ ገደቦች ተጥሰው ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ እንደሚሠራም መታወቅ አለበት፡፡

4) የጠላት ተላላኪ ሰርጎ ገብ ኃይል በሚጠረጠርባቸው አካባቢዎች በቅንጅት አሰሳ በማድረግና መረጃዎችን በየአካባቢው ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሰርጎ ገቦች የእምነት አባት፣ ገበያተኛ፣ ጸበልተኛ፣ ለሥራ የሚሰማራ፣ አርሶ አደር፣ የህልውና ዘማችና የከተማ ነዋሪ በመምሰል የመከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ኀይልና ሚሊሻ መለዮዎችን ለብሰው ከጸጥታ ኃይላችን ጋር በመመሳሰል አሳሳች መረጃዎችን በዘማቹና በኅብረተሰቡ ውስጥ ስለሚነዙ በትኩረት በመከታተል ለሚመለከተው አካል ማድረስ ይገባል።

5) ሰርጎ ገቦች ያለ እገዛ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ እድላቸው አነስተኛ ነው። በደረሱበት አካባቢ ገንዘብ እከፍላለሁ በሚል ማጭበርበሪያ የሽብር ተግባራቸውን ለማከናወን ይጥራሉ። ገንዘብ ተከፍሎትም ሆነ ተገድዶ መንገድ የመራቸውን አካል የሚፈልጉት ቦታ ከደረሱ በኋላ ይገድሉታል። ስለሆነም መሰል ሁኔታዎች ሲገጥሙ ፈቃደኛ አለመሆን አሊያም በሚያመች ሁኔታ የራስን የአርበኝነት እርምጃ መውሰድ ይገባል።

6) የጠላት ሰርጎ ገብ አንዱ ሥራ ከፍተኛ የጠላት ኀይል እየመጣ እንደሆነ ወይም ሰርጎ እንደገባ በማውራትና ማስወራት ሕዝቡና ዘማቹ ወገናችን እንዲሸሽ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያ እንዲህ ያለ ሽብር የሚነዙትን በማጋለጥ አካባቢን ባለመልቀቅና ከአካባቢው ሕዝብና ጸጥታ ኃይል ጋር ተናብቦ መረጃ በመቀያየር፣ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ የአርበኝነት እርምጃ በመውሰድ አሸባሪውን ማሳደድ ያስፈልጋል።

7) በሐሰት ስም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፍተው ለጠላት የሚሠሩ በአካባቢ ነዋሪ የሆኑ አካላትን ለሚመለከተው አካል መረጃ ማድረስ ያስፈልጋል። በሐሰት ስም ከሚፅፉት በተጨማሪ በስማቸው የጠላትን ዓላማ የሚደግፉ፣ ወገንን የሚጎዱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ በአካባቢ የሚኖሩ ግለሰቦችን ለጸጥታ ኀይላችን በመጠቆም የሰርጎ ገብን እንቅስቃሴ መከላከል ይገባል።

ሕዝባችን የተፈፀመበትን ወረራ ከሠራዊታችን ጋር በመሠለፍ ለመመከት የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ታሪካዊ ጠላታችን የሆነው አሸባሪ በክልላችን ቀብሩ እንዲፈፀም በቁርጠኝነት መታገሉን ሊገፋበት ይገባናል፡፡

ድል ለአማራ ሕዝብ !
ድል ለኢትዮጵያ !

የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ

ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም

Exit mobile version