Site icon ETHIO12.COM

በአሸባሪው ቁንጮ ፃድቃን ገ/ትንሣይ የሚመራው የጠላት ኃይል መመታቱ ተገለጸ

በአሸባሪው ቁንጮ ፃድቃን ገ/ትንሣይ የሚመራው የጠላት ኃይል በሰሜን ወሎ ግንባር በተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት መመታቱ ተገለጸ፡፡

Ethiopia : ዓርሚ ሁለት የሚባልና በከሀዲው ሜ/ጄ/ል ዮሀንስ፣ በምክትሉ ከሀዲው ማዕሾ በየነ እና ከሀዲው ከበደ ፍቃዱ እንዲሁም በሜካናይዝድ አዛዡ ከሀዲው ኮ/ል ገ/ስላሴ የተመራው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጠላት ሀይል ድባቅ መመታቱ ተገልጿል፡፡

በግንባሩ የተሰማሩ ሁለት ክ/ጦር አዛዦ እንደተናገሩት፣ መንግስት የተናጠል የተኩሥ አቁም እርምጃውን ካነሳ በኋላ ከበላይ በተሠጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ጋሸናን ዋና ማዕከል በማድረግ ከዋድላ እስከ ላልይበላ መስመር ላይ የነበረውን የአሸባሪውን ሀይል መደምሠሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጠላት በጀግኖቹ የሠራዊት አባላት፣ ልዩ ሀይል እንዲሁም የሚሊሻ አባላትና የአካባቢው አርሶ አደር ከበባ ውስጥ ሆኖ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

ይህ የተዳከመ የጠላት ሀይል በጋሸና፣ መቄት፣ ሙጃ፣ በንፋሥ መውጫ አካባቢዎች እየተመታና እየተበተነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በነዚህ አካባቢዎች በጠላት ላይ በተደረገ ጥቃት 3 ድሽቃ፣ 6 ሺህ የድሽቃ ጥይት፣ 87 የዕጅ ቦምብ፣ 229 ክላሽንኮቭ ነፍስ ወከፍ መሣሪያ፣ 5 ሺህ የክላሽ ጥይት፣ 1 የጦርሜዳ መነፅር ሲማረክ፣ በርካታ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል እና ጠላት ይጠቀምባቸው የነበሩ 2 መድፎች እንዲሁም አንድ ዙ 23 መደምሰስ መቻሉን ዋና አዛዦቹ ገልፀዋል ሲል የመከላከያ ሰራዊት ገልጿል፡፡

Exit mobile version