Site icon ETHIO12.COM

አገረ ስብከቶቹ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ አስገነዘቡ

በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስር አገረ ስብከቶች አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ የአሥር አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ለአሜሪካ የውጭጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ በወቅታዊ ጉዳይ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ እና አሜሪካ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ የሚጠይቅ የአቋም መግለጫ ደብዳቤ ዛሬ ማስገባታቸውን የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለኢዜአ ገልጿል።

ባለፉት ሠላሳ አመታት ዜጎች በማንነታቸው በሐይማኖታቸውና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግፍ ሲፈጸምባቸው እንደነበር ያመለከተው መግለጫው አሜሪካም ይህንን ግፍና ሰቆቃ ሲፈጽምና ሲመራ የነበረውን አካል ከመደገፍ እንድትታቀብ አሳስቧል።

ከዚህ በተጨማሪ አሸባሪው ህወሃት ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ አለም አቀፍ ህግን ሲጥስና ወንጀል ሲፈጽም ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ ሰፊ ዘገባዎች ቢሰሩም መረጃዎችን እንዳላየ የማለፍና በሽብር ቡድኑ የተፈጸመውን ወንጀል ከመጠየቅ ብሎም ጫና ከማሳደር አሜሪካ መቆጠቧን አመልክቷል።

በሌላ በኩል ሱዳን ይህንን ወቅት በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ቦታዎችን መያዟንና ንጹሃን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ያስታወሰው መግለጫው፤ ይህ ድርጊት የሁለቱን ወንድማማቾች ህዝቦች ለመለያየት የተደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ለዚህም አሜሪካ ሱዳን በሰላማዊ መንገድ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንዳታስወጣ ትብብር እንድታደርግ ጠይቋል።

አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ አሜሪካ ከምታደርገው ድጋፍ አጎዋ ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚያደርጉት ኢትዮጵያን መበታተን የሚፈልጉና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ናቸው ብሏል መግለጫው።

ለታሪካዊው የዓለም ቅርስ ቅዱስ ላሊበላም ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰላም መሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆም ነው የጠየቀው።

የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የአሜሪካና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም እምነቱን ገልጿል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ሰሜን አሜሪካ የጋራ ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን መግለጫ ያወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

ENA

Exit mobile version