Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪዎቹን አስወግደን የአገር ህልውናን ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን – በአሸባሪው ሸኔ ወንድማቸው የተገደለባቸው ወንድማማች ሠልጣኞች


አሸባሪዎቹን ህወሃትንና ሸኔን አስወግደን የአገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን ሲሉ በአሸባሪው ሸኔ የወንድማቸውን ህይወት የተነጠቁት ወንድማማች ወታደራዊ ሠልጣኞች ተናገሩ ።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ኦኬስትራ ቡድን በቡልቡላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በመገኘት ምልምል መሰረታዊ የወትድርና ሠልጣኞችን በሙዚቃ አነቃቅቷል።

በማዕከሉ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙት ሠልጣኞች መካከል ወንድማማቾቹ ጂሬኛ መገርሳ እና ኤሊያስ መገርሳ ይገኙበታል።

ሁለቱ ወንድማማቾች እንደሚናገሩት፤ በመጡበት አካባቢ አሸባሪው ሸኔ በሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግፍ በመፈጸም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ ጥሏል።

የሽብር ቡድኑ ከአሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ በመቀበል የእነርሱን ታላቅ ወንድም ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ክቡር ህይወት እንደነጠቀም ነው የሚገልጹት።

ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩትን ንብረት በመዝረፍ ህዝብን እያማረረ መሆኑንም ይናገራሉ።

አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የደቀኑትን አደጋ በመመከት ሀገርን ማሻገር እንደሚገባ የሚናገሩት ወንድማማቾቹ፤ እነርሱም ሀገራቸው ያቀረበችላቸውን ጥሪ ተቀብለው የመከላከያ ሰራዊቱን እንደተቀላቀሉ ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያ ልጆች እያሏት ለምን ህልውናዋ አደጋ ላይ ይወድቃል?” የሚሉት ወንድማማቾቹ፤ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ተቀናጅቶ ሀገር ከገጠማትን ፈተና እንድትሻገር ማድረግ እንዳለበት ይናገራሉ።

የአሁኑ ትውልድ እንደአባቶቹ ሀገርን ጠብቆ ለትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

የቡልቡላ ወታደራዊ ማስልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ኮሎኔል ታዱ እንዳለ በበኩላቸው ምልምል ወታደሮቹ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ወኔ የሚሰጣቸውን ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

አገርን ከየትኛውም ጥቃት መከላከል የሚችል ሠራዊት የመገንባቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ኮሎኔል ታዱ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version