Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ወረራና አፍራሽ ተግባራት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጎድተዋል

አሸባሪው ሕወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራና አፍራሽ ተግባራት ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በሰሜኑ የአገሪቷ አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ አሸባሪው ሕወሓት አሁንም በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራውን በመቀጠል በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አብራርተዋል።

በሁለቱ ክልሎች አሸባሪው ሕወሓት ያደረሰው የንብረት ውድመት እየተጠና መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በሁለቱ ክልሎች እያደረገ ባለው ወረራና ትንኮሳ እስካሁን ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ተጎጂ መሆናቸውን ነው ቢልለኔ የጠቆሙት።

በሁለቱ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ኮሚቴዎች በአፋርና በአማራ ክልሎች ተቋቁመው ከአጋር አካላት ጋር ሥራቸውን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ድጋፉ የሚፈለገውን ያክል አለመሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ወደ ትግራይ ክልል የሚጓዘውን የሰብዓዊ እርዳታ አሸባሪው ሕወሃት አሁንም መተላላፊያ ኮሪደሮችን እየዘጋና የማጓጓዝ ሂደቱን እያጨናገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተቸገሩ ዜጎች ወደ ክልሉ የሚላከውን ድጋፍም ቡድኑ ለታጣቂዎቹ እያከፋፈለ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም የሰብዓዊ ድጋፉን ሥራ ማስተጓጎሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ወደ ትግራይ የሚጓዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችም ጭነቱን ካራገፉ በኋላ በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ አለመመለሳቸው ሌላኛው ክፍተት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም በረድኤት ተቋማቱ ላይ ተጠያቂነት የሚያስከትል ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ጎን ለጎንም አንዳንድ የረድኤት ተቋማት መንግሥት ያስቀመጠውን የኮሚኒኬሽን መመሪያና ደንብ ባላከበረ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጓዳኝም እነዚህ የረድኤት ተቋማት በትግራይ ክልል የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢጠበቅባቸውም ያለማድረጋቸውን አስረድተዋል።

መንግሥት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች አሁንም የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ENA

Exit mobile version