Site icon ETHIO12.COM

ከሱዳን ሰርጎ ህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል የገባ የትህነግ ተላላኪ ተደመሰሰ፤ ” ምቱ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው”

በህዳሴ ግድባችን አካባቢ ሰርገው ለመግባትና ሽብር ለመፍጠር ያሰቡ ቡድኖች ላይ የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የማያዳግምና ለቀጣይ ትምህርት የሰጠ እንደነበር ተሰማ። ምቱ ያረፈበት ተላላኪ ትህነግ የላከውና ሱዳን ሰለጥኖ ወደ ህዳሴው ግድብ የተላከ ነበር።

መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ የጉምዝ ታጣቂዎችን ሽብርተኛው በሱዳን አሰልጥኖና አስታጥቆ በአልመሃል አቅጣጫ ጥቃት ለማድረስና የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ሙከራ አድርጎ እንደነበር ያስታወቂት የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተና ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ናቸው።

ጄኔራሉ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና በቀጣናው የተሰማሩ የክልል ልዩ ሀይሎች ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአሸባሪው ተላላኪዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ሀገር እና ህዝብን የሚያኮራ ጀብዱ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

በሽፍቶቹ ላይ በተወሰደው የማያዳግም እርምጃ የሰራዊታችን ጀግንነትና ፅናት ጎልቶ የታየበት አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት ዋና ሰብሳቢው ፤ በህዳሴ ግድባችን አካባቢ ጥቃት መሰንዘር እንደማይቻል ለሌሎች የውጭና የውስጥ ጠላቶችም ትምህርት ሰጥቶ ማለፉን ነው ያረጋገጡት።

የሰራዊታችንን ምት መቋቋም ያልቻለው ይህ የህወሀት አሽከር ሽፍታ ባረፈበት ከባድ ምት ተበታትኖ ወደ ሱዳን ደማዚን የሸሸ ሲሆን ፤ የአካባቢው ስጋት መሆን ወደ ማይችልበት ደረጃ ለማድረስ እግር በእግር እየተከታተሉ የመደምሰስ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጄኔራሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ ለደቂቃ ሳይቋረጥ በመካሄድ ላይ መሆኑን የገለፁት ጄኔራል አስራት የፀጥታውን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ሰራዊታችን ማንኛውንም መሰዋእትነት እየከፈለ እንደሚገኝና ይህን ለማድረግ አስተማማኝ ዝግጁነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።ባሳለፍነው ሳምንት በቀጣናው ሰራዊታችን ባደረገው ውጊያ ከ170 በላይ የጥፋት ሀይሎች መደምሰሳቸው ይታወሳል።

ፎቶግራፍ ፀጋዬ ገብሬ

Exit mobile version