Site icon ETHIO12.COM

አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ስትል ኢትዮጵያን እንድትደግፍ ጥሪ ቀረበ

ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ ለሚኖር ሰላምና እድገት አሜሪካ ኢትዮጵያን በመደገፍ አጋርነቷን ማሳየት እንደሚገባት የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደብዳቤ አስገብቷል።

በደብዳቤው አሁን በኢትዮጵያ የሚታየውን ችግር ለመረዳት ሀገሪቱ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የቆየችበትን የፓለቲካ ሂደት ማወቅ ያስፈልጋል ብሏል።

በነዚህ ዓመታት በኢትዮጵያውያን መካከል ቅራኔና መለያየት እንዲፈጠር በተለያዩ መንገዶች መሠራቱን አመልክቷል።

አሸባሪው ሕወሓት ይመራው በነበረው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የህዝብ ሀብት ዝርፊያ እንዲሁም በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞችና በግለሰቦች ላይ መንግስታዊ የሽብር ወንጀል ሲፈጸም ነበር ብሏል።

ህወሓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላም የሰላም ርሪን ረግጦ ወደ ጦርነት መግባቱንም አስታውሷል።

ባለፉት ሦስት ዓመታትም የቆየ ኔትወርኩን በመጠቀም ግጭቶች እንዲከሰቱ፣ ዜጎች ለሞት እንዲዳረጉና በአገሪቱ ሰላም እንዲደፈርስ መሥራቱን ነው ደብዳቤው ያስገነዘበው።

በመጨረሻ ጥቅም 24 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የፌደራል መንግሥትን በሀይል ከስልጣን ለማስወገድ መሞከሩን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱንና በመቀጠልም ለዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን እና የእርሻ ስራዎች እንዲሰሩ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሶ፤ አሸባሪው ህወሓት ግን ህጻናትን ለጦር በማሰለፍ ጭምር በአጎራባች ክልሎች ወረራ መፈፀሙን አውስቷል።

በበአማራ በአፋር ክልሎች በንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ በመፈፀም እና ንብረት በማውደም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ማፈናቀሉን ነው ያመለከተው።

በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት ገለልተኛ ሆኖ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነት በመረዳት ለአንድ ወገን ያደላ እይታውን እንዲያስተካክልና ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ ከማያደርገው ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ጫና እጁን እንዲያነሳ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በደብዳቤው መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version