Site icon ETHIO12.COM

ፀጋዬ በዚህ አይስማማም

በ1953 ፀጋዬ ገብረመድህን የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር(በአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር) ‘አርቲስቲክ ዳይሬክተር’ ሆኖ ተሾመ። በግዜው ብሔራዊ ከቲያትር ይልቅ የሆሊውድ ፊልሞች የሚታዩበት ቲያትር ቤት ነበር። አስተዳዳሪዎቹ አንድ አቋም ነበራቸው፦

“መንግሥት ምንም ድጎማ አያደርግልንም፤ የሰራተኛ ደመወዝ የምንከፍለው፣ ትያትር ቤቱንም የምናስተዳድረው የሆሊውድ ፊልሞችን በማሳየት በምናገኘው ገንዘብ ነው። ህዝቡ የሆሊውድ ፊልሞችን ይወዳል፤ ገንዘቡን ከፍሎ ገብቶ ለማየትም ፈቃደኛ ነው። ትያትር ለማየት፣ ገንዘቡንም ለመክፈል የሚፈቅድ ግን የለም”

“ህዝቡ ማየት የሚወደው ከሆሊውድ ፊልም ይልቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ቲያትሮችን ነው። ደግሞም ብሔራዊ ቲያትር የሃገሪቱ ትልቁ ቲያትር ቤት ነው። ግብሩም የጥበብ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ቲያትሮችን ማዘጋጀት እንጂ እርካሽ ፊልሞችን ማሳየት አይደለም” የሚል ፅኑ እምነት ነበረው።

ፀጋዬ ረዣዥም ግጥሞችን መፃፍ፣ ባለ አንድ ገቢር ተውኔቶችን መድረስ፣ ከአለም ታላላቅ ተውኔቶችን እየመረጡ መተርጎም የዘወትር ግብሩ ነበር። ነገር ግን የፀጋዬ አላማ ከዚህም ላቅ ያለ ነበር። ፀጋዬ የቲያትርን የክብር ደረጃ ማረጋገጥን ግብ አድርጎ ይዞ ነበር። እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ለስእልና ቅርፃቅርፅ ያደረጉትን እርሱም ለቲያትር ማድረግ ምኞቱ ነበር።

ወደ ብሔራዊ(ቀኃስ) እንመለስና ፀጋዬ “ሀሁ በስድስት ወር”ን ፃፈ። በቲያትር ቤቱም ለህዝብ ቀረበ። ከሆሊውድ ፊልሞች ተመልካች የበለጠ አገኘ። ፀጋዬ የህዝብን ልብ ከፊልም ወደ ቲያትር መለሰ።

ብሔራዊ ቲያትር ተራ የሰፈር ቪዲዮ ቤት ሆኖ ነበር። መድረኩ ታላላቅ ተዋናዮች የሚንጎማለሉበት ሳይሆን የአቡጀዲ ግርግር የሚታይበት ቦታ ሆኖ ነበር።

ቲያትር በዘመኑ ተዋርዳ ነበር። በርካሽ የሆሊውድ ፊልሞች ተደፍጥጣ ነበር። ፀጋዬ ትያትር ከተናቀችበት አክብሮ፣ ከተጣለችበት አንስቶ፣ ከተረሳችበት አስታውሶ፣ ከተጎሳቆለችበት አስውቦ፣ ከጓዳ ወደ ሳሎን፣ ከመቃብር አስነስቶ ዳግም መድረክ ላይ ሰቀላት። ነፍስ ዘራባት።

የመንግሥት ድጎማ ሳይጠብቅ፣ ግዙፉን እና ሃያሉን ሆሊውድ በብእሩ ብቻውን ተፋልሞ ያሸነፈ ጀግና አለ። ስሙም ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ይባላል።

Via book for all

Exit mobile version