Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ በ”ተክደናልና መገንጠል” ቀውስ ተወጥሯል – ሪፖርት

በትግራይ ፖለቲካ ገና ከጅምሩ ቸግሮችን በውይይት ለመፍታት ፋልጎት ያላቸውን ” ጸረ ትግራይና ባንዳ” የሚል ስም ይሰጥ ነበር። ወደ አገረ ማሪያም ዋሻ አምርቶ ከስምንት ወር በሁዋላ ወደ መቀለ የተመለሰው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አመራር፣ ትግራይን ማስተዳደር ሲጀምር በርካታ ሰዎችን ስፍራ መርጦ ማጥቃቱ ይፋ መሆኑም ይታወሳል። ” ብልጽግናን አግዛችዃል፤ ባንዳ” በሚል ስም መሆኑ ነው። ለዚህ ክስ ትህነግ ይፋዊ መልስ አልሰጠም። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ግን ስምና ማንነት፣ እንዲሁም አካባቢ ጠቅሰው ብዙ ብለዋል።

በመከላከያ ሰራዊት ላይ ” በክህደት የተፈጸመ” በተባለው ጥቃት ሳቢያ ” የህግ ማስከበር ዘመቻ” ተብሎ እጅግ ፈጣን ማጥቃት ተደርጎ የትህነግ ሃይል ሲሸነፍ፣ ከሞት የተረፉና ያልተማረኩት አመራሮች ወደ አገረ ማሪያም ሲያመሩ ተቀናቃኝ የነበሩ የፓርቲ አመራሮችም ” ቅድሚያ ትግል” በሚል ተቀላቅለዋቸው ነበር። የትግራይ ነጻነት ፓርቲ አመራር አቶ መሓሪ ዮሃንስ በቅርቡ በትግርኛ ባደረገው ቃለ ምልልስ ” ተክደናል” የሚል ሙሉ ይዘት ያለው ጉዳይ አንስቶ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

አቶ መሓሪ የትህነግ አመራሮች ወደ መቀለ ከተመለሱ በሁዋላ እንደገፉዋቸው ወይም ” እኛ የተመረጥን ነን” በሚል የጠበቁትን ያህል በክልሉ የአመራር ተሳትፎ እንደተነፈጉ አምርረው ተናግረዋል። የትግራይን መጻዒ እድል አስመክቶ ” ትህነግ ሪፈረንደም ቢባል ምን እንደሚልና እንደሚቀሰቀስ በግልጽ ይንገረን” ሲሉም በትህነግ ውስጥ የትግራይ የመገንጠል ጥያቄ እንዴት እንደተያዘ መረጃ እንዲጠራ ጠይቀዋል።

ሰሞኑንን ይፋ የሆነውና በምስከረም 2013 የተዘጋጀ እንደሆነ የተነገረለት 88 ገጽ የትግል ስትራቴጂ ሰነድ እንደሚያስረዳው ከተቻለና የትህነግን ምኞት የሚያስጠብቅ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል፣ ካልሆነ አገር የመሆን አጀንዳን ተግባራዊ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ነገሮች አልሄዱም። 2ሚሊዮን ሰራዊት እንዳዘጋጀ የሚጠቅሰው ስትራቴጂ ባሰበው መልኩ ባለመሄዱ ይመስላል አሁን ላይ ሁለት ሃሳብ እየተነሳ ነው። ስትራቴጂው አለመሳካቱ ስትራቴጂውን ማዕከል አድርጎ ለህዝብ ሲነገር በነበረው የቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳ ሳቢያ ነው ልዩነቱ የተነሳው።

ለዚህ ሪፖርት ያናገርናቸው እንደሚሉትና “የትግራይ መከላከያ ሃይል” የሚባለው ሰራዊት አመራሮች በዚህ ሁለት ሃሳብ ውስጥ አሉበት። እንደሚታወቀውና ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በማኒፌስቶ በግልጽ እንደተቀመጠው ትህነግ ኢትዮጵያን እየመራም ቢሆን ዓላማው ትግራይን አገር ማድረግ ነበር። በተቋቋመለት ዓላማው መሰረት አገር ለመሆን ካስቀመጠው ጊዜ ፈጥኖ ለውጥ የገነደሰው ትህነግ፣ በፍጥነት ወደ ስልጣን ለመመለስ በየአቅጣጫው ሲረባረብ እንደነበር ይፋ የሆነበት ስትራቴጂው ምስክር ይሆናል። ይህ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት ስቃይዋን እንድታይ፣ ዜጎች ሰላም እንዲያጡ፣ አገሪቱ እንድትበጠበጥ፣ ዙሪያው እንዲናጋ ሲሰራ የነበረው ትህነግ ስለመሆኑም ማረጋገጫ መሆኑ እዚህ ላይ ይሰመርበታል።

ዛሬ ላይ በትግራይ ሃይል መሪዎችና አዋጊ መኮንኖች ዘንዳ የሃሳብ ልዩነት ያስነሳው ጉዳይ የትግራይ መገንጠል ጉዳይ ነው። ለጊዜው ስማቸው የማይገለጹ የትጋይ አካባቢዎች ስለ መገንጠል መስማት እንደማይፈልጉ ይሰማል። መገንጠልን በገሃድ ሲሰብክ የነበረው ትህነግም ቢሆን በውስጡ መገንጠልን አስመልክቶ ተመሳሳይ አቋም እንደሌለው ይነገራል። አብዛኛው ወጣት መገንጠልን ይደግፋል እየተባለ ነው። ይህ ክፍል ግን መገንጠል ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ለመገንጠልና አገር ለመሆን ቢያንስ መሟላት የሚገባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች በውል ያልተረዳና በፕሮፓጋንዳ የሚገፋ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ከትህነግ ውጭ ያሉ አብዛኛው ፓርቲዎች የዛሬ አቋማቸው ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም መገንጠልን የሚያቀነቅኑ እንደነበሩ በተደጋጋሚ ይፋ አድረገው ነበር።

ያነጋገርናቸውና የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ የሚከታተሉ ሲናገሩ ትህነግ አመራሩ ወደ መቀለ ከመመለሱ በፊት ከሁሉም ተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮች ጋር በቁርኝት ይሰራ ነበር። አቶ መሓሪ እንዳሉት መቀለ ከተመለሰ በሁዋላ ፊት ነስቷቸዋል። በዚህ ሳቢያ ስማቸውን የማይጠቅሷቸው ክፍሎች ከተወሰኑት የትግራይ ወታደራዊ ሃይል መሪዎች ጋር የሃሳብ ስምምነት አድርገዋል። ይህም ማለት ትግራይ አገር እንድትሆን አቋም ይዘዋል።

ትህነግ አሁን ላይ መገንጠልን ማቀነቀን ዋጋ እንደሌለው በውስጥ ያምናል። ከወታደር ክንፉ የተወሰኑ አመራሮች ይህን ይደግፋሉ። ትህነግ አደባባይ ለቅስቀሳ ሲል እንደሚለው ሳይሆን ” አሁን ስለመገንጠል ከውሰን ከያዝናቸው ስፍራዎች ተነቅለን ትግራይ እንቀረቀራለን” ሲል በውስጥ ምክንያት እንደሚያቀርብ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይገልጻሉ። በሌላ አነጋገር አሁን ባለው ሁኔታ መገንጠልን ማቀነቀን አዋጪ እንደማይሆን ተህነግ ውስጥ ዕምነት አለ።

ሕዝቡን ለማነሳሳት ሲቀርቡ የነበሩ የአገርነት እሳቤዎች እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ሳይሆን በሌላ መንገድ ተግባራዊ ይሁን ከተባለ ራሱ ትግራይ ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል የሚገምቱም አሉ። ሰለሞን ሃይሌ እንደሚለው “ትግራይ ዛሬ ምንም ነገር የመሸከም አቅም የላትም” ሰለሞን ሲቀጥል ” የምፈራው የጥላቻው መካረር ሌላው ሕዝብም አንፈልግም ወደሚልበት ደረጃ እንዳይደርስ ነው” ይላል። ሰለሞን “ትግራይ ራስዋን ትቻል” የሚል እንቅስቃሴ ሊጀመር እንደሆነ መስማቱን ገልጾ ሁሉም ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ይመክራል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ከተቋቋመ ጀምሮ በበረሃ በቆየባቸው፣ ከኤርትራ ጋር ዳግም በተካሄደ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሳቢያ በተደረግ ጦርነት በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን አጥተዋል። በትግራይም ዛሬ ድረስ ቤሰብ ልጅ እየጎደለበት ነው። ወደ አማራና አፋር ክልል የሰፋው ጦርነት ያስከተለው ድፍን ቀውስ ለሰሚ ግራ የሚጋባ ነው።

በትግራይም ሆነ በአማራና አፋር ክልል የደረሰው ቀውስና ውድመት፣ ሰብአዊ ጥፋት አገሪቱን ወደ ከፋ ጎዳና እያመራት፣ በየአቅጣጫው እየፈጠረ ያለው ስሜት መበላሸት አሳሳቢ ሆኗል። ትግራይ ከሚያዋስኗት አማራ፣ አፋር፣ ኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ተበላሽቷል። በመሃል አገርም ያለው ስሜት ጥሩ አይደለም። አሁንም ስሜትን የሚያበላሹ በልዩነት አብሮ መኖር እንዳይቻል የሚያደርጉ ተግባራት እየተፈጸመ ነው። ሁሉም ወገን እገሌ ከገሌ ሳይባል እንዴት ከዚህ ቀውስ መውጣት እንደሚቻል አይገባውም።

ሰለሞን እንደሚለው ” በትህነግ የግማሽ ምዕተ ዓመት ሴራ መረረን” የሚሉ ድምጾች ገነዋል። በትግራይም ” በቃን አገር እንሁን” የሚሉ ይበዛሉ። ከሁሉም ወገን ፖለቲከኞች የህዝቡን ስሜት መግታት የሚችሉበት አቅም ያላቸው አይመስልም። እርቅም ሊሆን የሚችል የማይመስለው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ በህግ የምትፈልጋቸውም ዕርቅን አይመኙም። ዕርቅ ፍትህም ስላለበት።

አሜሪካ በጃጁት መሪዋ ፊርማ ይፋ ያደረገችው የተጨማሪ ማዕቀብ ጉዳይ ድርድርን ማዕከል ያደረግ ቢሆንም ” እንዴት?” የሚለውን ጥያቄ አይመልስም። ጦርነቱን የሚያባብሱትን እንደሚቀጣ የሚያትተው የአሜሪካ ዛቻ ” የአገር መከላከያ ያረደና ፣ ማረዱን በጀግንነት በፊትለፊት ያወጀውን አካል” ጭራሽ አያነሳቸውም። አንድ ወታደር ተነካ ብለው ከተማና ህዝብ የሚያወድሙት ኢምፔሪያሊስቶች ” ስለምን ኢትዮጵያን እንዲህ እንደሚጫኑ አይገባንም” ሲሉ ዜጎች ቢጠይቁም ቁርጥ ያለ ምላሽ የለም።

ኤርትራ፣ አማራ፣ መንግስትና ትህነግን ቀውስ በማስፋፋት እንደሚጠይቅ ይፋ ያደረገው የጆ ባይደን ማስፈራሪያ ውጤት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ብዙም ትኩረት ያልሳበው በትግራይ መገንጠልና አለመገንጠል አጀንዳ ላይ የሚንሸራሸረው አቋም ” ለጊዜው ይቆይ፣ ይከፋፍለናል” በሚል ቢታሸግም እየበሰለ መሆኑ ይሰማል። የትግራይ ዳያስፖራ ” ለጊዜው እንተወው” ያለውና አቶ መሃሪ ይፋ ያደረጉት ጉዳይ በመሃል አገር ህዝብ ተደግፎ ” ትግራይ ትገንጠል” የሚለው ግፊት መንግስት ላይ እንዳይጠና ስጋት አለ። ምክንያቱም አብዛኞች በገሃድ እንደሚሉት በሁሉም አቅጣጫ የሚሰራጨውና ሲሰራጭ የኖረው የፕሮፓጋንዳው ክፋት አብሮ ያያዘውን ስር ቆራርጦታል። የአብሮነት ስሜቱን ገድሎታል። በሁሉም ወገኖች ” እንዴት አንድ ገበታ እንቀመጣለን” የሚሉም ጥቂት አይደሉም።

“ኢትዮጵያዊ አይደለንም” በሚል በግልጽ አቋማቸውን የገለጹ የመኖራቸውን ያህል፣ ” አንፈልጋችሁም” የሚሉም ሚልዮኖች ናቸው። በዚህ ሁለት የከረረ መስመር ምስኪኖች ዋጋ እየከፈሉ ነው። የትግራይ ፖለቲካ ከቀድሞ ጀመሮ የጸዳና ጥርት ብሎ የሚሄድ ባለመሆኑ ከጥርጣሬ ርቆ አያውቅም። አሁንም አሁኑኑ ” እንለይ” በሚሉና ” ቆይ ትንሽ” የሚሉ ሁለት በጊዜ ገደብ የሚጣሉ፣ ግን ተመሳሳይ ፍላጎቶች ናቸው። ለሁሉም አቶ መሓሪ እንዳሉት፣ ከሌሎችም እንደሚሰማው ትግራይ ከገባችበት ቀውስ በላይ ትገንጠል” የሚለው ንትርክ መጨረሻው ምን ይሆን?

Exit mobile version