Site icon ETHIO12.COM

145 ሰላማዊ የገጠር ነዋሪዎች የጉሙዝ ታጣቂዎች አገተ

በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራውና የሚረዳው የጉሙዝ ታጣቂዎች በሴዳል ወረዳ 145 ሰላማዊ የገጠር ነዋሪዎችን ማገታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከልና ካማሺ ዞኖች የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ መፍጠን እንዳለበት አሳሳበ።

ኢሰመኮ በቤኒንሻንጉል ካማሺ ዞን የሚገኘው የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጾ፣ በክልሉ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግስቱና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሴዳል ወረዳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

በዚህ ችግር ምክንያትም ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን የኢሰመኮ መግለጫ ያስረዳል።

ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ብለው የሚጠሯቸው ኃይሎች በወረዳው የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አባወራዎችን (ቤተሰቦችን) ማገታቸውን ከዚሁ ሁኔታ የሸሹ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

ታጣቂዎቹ “ዓላማችንን አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት አፍሰው እንደወሰዷቸውና በተለምዶ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸው አክለው አስረድተዋል።

ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸውንም ከነዋሪዎቹ ማረጋገጡን ኢሰመኮ ገልጿል።

በመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በደረሰው ጥቃት ምክንያት 5 ሺህ የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉም ብሏል።

ኢሰመኮ አደረኩት ባለው ክትትል፣ ከመስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” በመካሄድ ላይ ነው ብሏል።

እንዲሁም ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የሴዳል ወረዳ አመራሮችም ሆነ ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ አለመሆኑን ከነዋሪዎቹ ሰምቻለሁ ብሏል።

በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ የጣሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቢቆዩም፣ በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች አደጋውን ለመቀልበስ እና የሲቪል ሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በቂ አለመሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰቡን ያመለከተው ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።

Exit mobile version