Site icon ETHIO12.COM

በፌዴራል ደረጃ በሕዝብ የተመረጠው አዲስ መልመንግሥት ይመሠረታል

 በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በሕዝብ የተመረጠውና እንደገና የተዋቀረው አዲስ መንግሥት ዛሬ በፌዴራል ደረጃ ይመሠረታል።

የኢፌዲሪ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምስረታና የመክፈቻ ጉባኤ ዛሬ እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቋል፡፡

የምክር ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን÷ የጉባኤው ሂደትም በቀጥታ ስርጭት በሚዲያ እንደሚተላለፍ አስታውቋል፡፡

የፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ንግግር የዘንድሮውን በጀት ዓመት የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚያመላክት ነው የሚጠበቀው።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት፥ በሕዝብ ተመርጦ አዲስ የሚቋቋም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜውን መጀመር ያለበት በ“መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ነው” ብሎ በደነገገው መሠረት ነው ነገ በፌዴራል ደረጃ አዲስ መንግሥት የሚመሠረተው።

በመስራች ጉባኤው ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

በተለይም የሕዝብ ተውካዮች ምክር ቤት በሚያካሂደው መስራች ጉባኤው፥ ከአባላቱ መካከል ምክር ቤቱን የሚመሩ ዋና እና ምክትል አፈ ጉባኤዎችን እንዲሁም የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው፥ በምክር ቤቱ የተመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትርም የሚኒስትሮች ምክር ቤት (የካቢኔ) አባሎቹን በሕዝብ ከተመረጡ የምክር ቤት አባላት ወይም ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለስቦች መካከል የመረጣቸውን ዕጬዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስጸድቃል።

FBC

Exit mobile version