Site icon ETHIO12.COM

ሕዝብ ተገዶ ዝርፊያ እንዲያካሂድ ተደርጎ ቪዲዮ ሲቀርጽ ነበር

የጁንታው ቡድን አባላት በንፋስ መውጫና አካባቢው ተባረው እስኪወጡ ድረስ በቆዩባቸው ጊዜያት በርካታ የመንግሥትና የህዝብ ተቋማትን ዘርፈዋል፤ በወቅቱም የሚፈልጓቸውን ንብረቶች ከወሰዱ በኋላ ነዋሪውን በማስገደድና “ዝረፉ” እያሉ ምስል ይቀርጹ እንደነበር በወቅቱ በንፋስ መውጫ ከተማ የነበሩ የአይን እማኞች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል።

የወራሪው ቡድን እራሱ ዘራፊና ንብረት አውዳሚ ሆኖ በተገኘበት ስፍራ ‹‹ እኔ ሳልሆን ህዝቡ እራሱ ነው የዘረፈው ››የሚል ፕሮጋንዳ ለመጠቀም አስቦ የካሜራ ቀረጻ ማካሄዱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የንፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪው አቶ ደሴ ውዴ ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ለጥቂት ቀናት በአካባቢው የቆየው የወራሪው ቡድን በርካታ የመንግሥት፣ የግለሰብ እና የአርሶ አደር ንብረት የሆኑ ዩኒየኖችን ዘርፏል። በወቅቱ ከጤና ኬላዎች፣ ከኮሌጆችና ከተለያዩ ቢሮዎች ማሽኖችን እና አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ንብረቶች ጭኖ ወስዷል።


READ MORE NEWS

በኋላም የተወሰኑ ዕቃዎች ሲቀሩት ህዝቡን በማስገደድ ቢሮዎቹን ገብተው እንዲዘርፉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የተገደደው ኗሪ ወደየቢሮዎች እና አገልግሎት መስጫዎች ገብቶ እቃ እየያዘ እንዲወጣ ሲገደድ የጁንታው አባላት ቪዲዮ ይቀርጹ ነበር፤ ይህም ንብረቱን የወሰደው ህዝቡ እንጂ እኛ አይደለንም የሚል የፖለቲካ ጨዋታ ለማራመድ ነው ብለዋል።

በወቅቱም ወራሪው ቡድን ዕቃዎችን ሲያጓጉዝበት የነበረባቸው አረንጓዴ ተሳቢ መኪናዎች አሁን እንደ ምንሰማው የእርዳታ እህል ወደትግራይ ለማስገባት በሚል የገቡ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ነው የአይን እማኞቹ የሚያስረዱት ። ‹‹ይህም አሸባሪ ቡድኑ የሰብአዊ አገልግሎት መስጫዎችን ለወንጀል እየተጠቀመበት መሆኑን ያሳያል። ከዚህ ባለፈ ህዝቡን በግዳጅ አስወጥተው የደገፋቸው በማስመሰል እንዲቀረጹ አድርገዋል፤ እኔም በግዳጅ አንገቴን አንቀው ወደከተማው መናኸሪያ ከወሰዱኝ በኋላ ህዝብ መሃል ቀርጸውኛል›› ሲሉ አቶ ደሴ ተናግረዋል።

ሌላኛው የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪ አቶ ነጋ ደሳለኝ በተመሳሳይ በወራሪው በግዴታ ምስላቸው የተቀረጹ ሰው ናቸው። ቡድኑ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የቪዲዮ ቀረጻ አለው በወቅቱ ዲሽቃ እና ክላሽ መናኸሪያው ውስጥ ጠምደው በርካቶችን ቀርጸዋል። እኔንም መናኸሪያው ውስጥ ከሰበሰቡት ህዝብ መሃል አውጥተው የደገፍኳቸው በማስመሰል እንድናገር አድርገዋል። ከዚህ ባለፈ ግን የአገልግሎት መስጫ ተቋም ውስጥ ገብተው ከዘረፉ በኋላ ህዝቡን በግዳጅ እንዲገባ እያደረጉ ምስሉን ቀርጸውታል። ይህም ህዝብና ህዝብ ለማጣላት ህዝብና አስተዳደሩን ለማጋጨት በማሰብ ነው ብለዋል።

በወቅቱ የነበሩት የአይን አማኝ ነጋዴዎቹ አቶ አላምረው አበበ እና አቶ ማስሬ አበራ የወራሪው ቡድን ተንኮል ረቂቅ ነው ይላሉ፤ በየአካባቢው ዘርፈው በከባድ መኪናዎቻቸው ከጫኑ በኋላ ህዝብን አስገድደው እቃ ውሰድ ይላሉ። ህዝብ በግዳጅ ሲያነሳ ቪዲዮ ከቀረጹ በኋላ ደግሞ መልሰው ያስገደዱትን ህዝብ የያዘውን እቃ ቀምተውት ይወስዳሉ። ቪዲዮ ላይ ህዝቡ ዘረፈ ለማስባል ያላደረጉት ጥረት የለም።

‹‹ወራሪው ቡድኑ ነፋስ መውጫ ላይ የቀረጸውን ቪዲዮ እስካሁን ያልለቀቀው በዘረፋ ሲጠየቅ እኔ ሳልሆን ህዝብ ነው ብሎ ለማሳየት እንደሆነ ይጠበቃል። በዚህ መልኩ የተቀነባበረ ዘረፋ በርካታ አገልግሎት መስጫዎች እና የግል ድርጅቶች ወድመዋል። እኛም የንግድ ሱቃችን ሙሉ በሙሉ ተዘርፎ ነበር፣ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በብድር ሱቃችንን አደራጅተን ሥራ ጀምረናል›› ሲሉ ተናግረዋል ።

ጁንታው የዘረፈውን እቃ የሚያጓጉዝበት ተሽከር ካሪዎች በእርዳታ ስም ወደትግራይ ክልል የሚገቡ ተሳቢዎች እና ሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎች ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ ይህን ወንጀል ሲፈጽም በተቀናጀ እና ሆን ብሎ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ለመስራት ዝግጅት አድርጎ ነው፤ ይህንንም ድርጊት በሀገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያሉ ዜጎች ሁሉ ሊቃወሙት ይገባል ብለዋል የአይን እማኞቹ።

ጌትነት ተስፋ ማርያም አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም



Exit mobile version