Site icon ETHIO12.COM

ሐይቅ ከተማ በማን እጅ ናት?

የሰሜን ሸዋን በከፊል መቆጣጠራቸውን በግልጽ ማንነታቸው የማይታወቁ የትህነግ ሰዎች በማህበራዊ ገጾቻቸው እየለጠፉ ባለበት ወቅት ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ ሃይቅ፣ ቢሲቲማ ከተሞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል። አማራ ማስ ሚዲያ በበኩሉ ዛሬ ማለዳ ላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ውጊያ እየተደረገ መሆኑ አስታውቆ። ይህ እስከታተመ ድረስ ሃይቅ በትህነግ እጅ እንዳልገባች አረጋግጧል።

“ትናንት ማምሻውን ሐይቅ ከተማ በጠላት እጅ እንደወደቀች ተደርጎ በአንዳንድ የጠላትን አጀንዳ በሚያራግቡ ቅጥረኛ ኃይሎች ሲቀርብ የነበረው የበሬ ወለደ አሉባልታ ሐሰት ነው። ሐይቅ ከተማ አሁንም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቁጥጥር ሥር ስትሆን የዞን፣ የተሁለደሬ ወረዳና የሐይቅ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው አመራር በመስጠት ላይ ይገኛሉ” ሲል የአማራ ማስ ሚዲያ አመልክቷል።

አቶ ጌታቸው ወደ ኮምቦልቻና ደሴ እየገሰገሱ እንደሆነ በቲውተር ገጻቸው ቢያመልከቱም እስካሁን ከነጻ ወገን ማረጋገጫ አልወጣም። አቶ ጌታቸውን ቀድመው ሰሜን ሸዋን በከፊል እንደተቆጣጠሩ የትህነግ ሰዎች በውል በማይታወቅ ማንነት በማህበራዊ ሚዲያዎች እያሰራጩ ነው። ይሁን እንጂ በተጠቀሱት አካባቢዎች ለጊዜው ምን እንደሌለ እማኞች አስታውቀዋል።

” አሸባሪው፣ ጨፍጫፊው፣ ዘራፊውና ወራሪው የትህነግ ኃይል በውጫሌ፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦና ደላንታ ግንባሮች ጦርነት የከፈተ ቢሆንም ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ሰርጎ ለመግባት እየሞከረ ያለውን ወራሪ ኃይል ወደ ቀሪ አካባቢዎች እንዳይገባ በአንድነት በመዝመት መመከት እንዲሁም አካባቢውን ከጸጉረ ልውጥ በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ” በቀረበለት ጥሪ መሰረት ከጠላት ሃይል ጋር ትንቅንቅ ላይ እንደሚገኝ የደቡብ ወሎ አስተዳደር ገልጿል።

በአዲስ አበባ ሕዝብ “ወገኖቻችን እያለቁ ነው መንግስት ሙሉ ክተተ በመላው አገሪቱ ሊያውጅ ይገባል” የሚሉ ወገኖች ሕዝባዊ ሰልፍ አዘጋጅተው መንግስትን ለመጠየቅ ዝግጅት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።

ከአዲስ አበባና ከተለያዩ ከተሞች ሆነው በድብቅ ማንነት ባምህበራዊ ሚዲያዎች የሃሰት መረጃ የሚያሰራጩ ክፍሎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል። ከዚህ ቀደም ኢንሳ ጥናትና ክትትል አድርጎ እንዲህ ባለው ተግባር ላይ የተሰማሩት በሃሰተኛ ስም የሚጠሩ የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደሆኑ አርጋግጦ ነበር። ይሁን እንጂ አካባቢውን አላስታወቀም።

Exit mobile version