Site icon ETHIO12.COM

“የሰው ጎርፍ የሚጎርፍበትን ጦርነት ከጀርባው ማምከን አዲሱ ስሌት ሆኗል”

የአገር መከላከያ ሰራዊት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀው ትህነግ የሚከተለው የጦርነት ስልት ኢመደበኛ ነው። የሰው ማዕበል በማጉረፍ የሚደረግ ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት እጅግ ኋላ የቀረ ቢሆንም ጀነራል ጻድቃንን ” ስትራቴጄስት” ሲሉ ቢቢሲ አማርኛውን ጨምሮ በዓለም ታላላቅ በሚባሉ ሚዲያዎች የተሞገሱበት ስልት ሆኗል። ይህንኑ ስልት ለማምከን “የሰው ጎርፍ የሚጎርፍበትን ጦርነት ከጀርባው ማምከን አዲሱ ስሌት ሆኗል” እየተባለ ነው።

በዚህ የውጊያ ዘዬ እስከ ጋይንትና ደብረታቦር መዳረሻ ሰው አጉርፎ ገብቶ የነበረው ወራሪ ሃይል፣ ይህንን ወረራ ሲያካሂድና ከወረራቸው አካባቢዎች ሲለቅ ምን ያህል ሰብአዊ ዋጋ እንደከፈለ እስካሁን በውል አልታወቀም። መንግስት ከወራት በፊት እንዳስታወቀው በአስር ሺህ አልቀውበታል። እነሱ ይፋ እንዳደረጉት ደግሞ ኢትዮጵያ ስንት ወታደር እንዳላት ባይታወቅም ሰባ ሺህ በላይ ወታደር መግደላቸውን አስታውቀዋል።

ምንም ሆነ ምን በጎንደር ወደ ባህር ዳር ለመቁረጥ የተሞከረው ሙከራ ሳይሳካ በመቅረቱ ” ጦርነቱን በቀናት ግፋ ቢል በሳምንታት እንጨርሰዋለን” በሚል በይፋ ካስታወቁ በሁዋላ በደሴ ግንባር ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ በይፋ እየተገለጸ ነው። ሃይቅን አልፈው ወደ ኮምበልቻና ደሴ እየገሰገሱ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ረዳ ” ትግራይ ታሸንፋለች” በሚለው መፈክር በተዘጋ መልዕክታቸው ከአምስት ቀን በፊት አስታውቀው ነበር። ደጋፊዎቻቸውም ” በመጨረሻ ደሴ” በሚል ፖስት ማህበራዊ ገጾችን አስውበው ነበር። በሁዋላ ላይ አነሱት እንጂ።

ይህንኑ ተከትሎ በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ እንዲሁም በመላው አማራ ክልል በተላለፈ የክተት ጥሪ ሰፊ ቁጥር ያለ ሕዝብ ወደ ግንባር መትመሙን የመንግስትና የግል ሚዲያዎች በምስል እያስደገፉ እየዘገቡ ነው። ከጎንደርና ጎጃምም ወደ ደሴ ግንባር የተንቀሳቀሱ ግንባር ያለውን ሃይል ሲቀላቀሉ ታይቷል። ያለ ምንም ማጋነን የትህነግ ሃይል በሰው ጎርፍ እየተርመሰመሰ ወደፊት መምጣቱ አስግቶ ነበር።

እሾህን በሾህ እንዲሉ ሕዝብ ከማነቃነቅ ጀምሮ ባለፉት አስራ አንድ ወራት ያተሰማ አዲስ ጥቃት መጀመሩን የመንግስት ሚዲያዎች፣ የመንግስትን ሃላፊዎች ጠቅሰው መዘገብ ጀመሩ። የአየር ጥቃት ተጀመረ። እንግዲህ ይህ ጥቃት ነው “ከጀርባ ማመከን” የተባለው።

መከላከያ አዲስ የጦርነት ስልት በመከተል ሎጅስቲክና ተተኪውን ሃይል ከመንገድ የማስቀረት፣ ማስለጠኛና መሳሪያ ማቀናበሪያን ማጥፋት እንዲሁም የግንኙነት አውታሮችን የመምታት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ የጭፍራውንና የደሴ ግንባሩን ስያካትት አራት ” ውጤታማ” የተባሉ የጥቃት ኦፕሬሽኖች በመቀለ ዙሪያና አቅራቢ መካሄዳቸውን አስታውቋል።

ከትናንት በስቲያ አቶ ጌታቸው “ተቆጣትረነዋል” ባሉት አካባቢ የተፈጸመው ጥቃት ይፋ ሆነ። “በወረባቡ በኩል ቆርጦ ለማጥቃት የሞከረውና ከጎሃ ት/ቤት አካባቢ ጀምሮ የተለያዬ ሎጀስቲክስ እና የሰው ኃይሉን አከማችቶ የነበረው የአሸባሪው ሃይል አየር ኃይላችን በወሰደው እርምጃ፣ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የጠላት ተሽከርካሪ እና የሰው ኃይሉ ላይ እርምጃ ተወስዶአል። በዚህ አካባቢ የአርሶአደሩን በሬ አርዶ ሲበላ የነበረው አሸባሪ ሓይል አየር ሓይላችን በወሰደው እርምጃ ከነተሽከርካሪው እንደወደመ ዘጋቢዎቻችን አረጋግጠዋል” ሲል አዲስ ዘመን የአዲሱን የውጊያ ስልት ውጤት አስፍሯል።

በግንባር ያሉ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለሙያዎች ቦሩ ስላሴ አካባቢ ጥቃት ለመሰንዘር የገባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአሸባሪው ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ በመከላከያ፡ በአማራ ልዩ ሃይል፡ ሚሊሻና ፋኖ መድምሰሱንም አስታውቀዋል። እነዚህ ስፍራዎች አቶ ጌታቸው በትህነግ ሃይል ስር የወደቁ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር።

ደሴና አካባቢውን ለማተራመስ ያቀደው በርካታ ቁጥር ያለው የአሸባሪው ታጣቂ ቦሩ ስላሴ ላይ ሙሉ በሙሉ የተደመሰሰው በአየር ሃይሉ ሙሉ እገዛ ሲሆን፣ ከሰሞኑ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችና ዲጅታል ሰራዊታቸው ደሴና ኮምቦልቻን ተቆጣጥርን ከሚለው ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ቀጠሮ በተያዘለት ጊዜ ሳይስካ መቅረቱን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመልክታሉ።

ሕዝብ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣና ቀውሱ እንዲባባስ ሀሰተኛ መረጃዎች በማሰራጨትና በሰርጎ ገቦች አማካኝነት ውዥንብር ከመፍጠር ባሻገር በርቀት ንጹሃን ላይ በተኮሱት ከባድ መሳሪያ ከ30 በላይ ንጹሃን ውጫሌ ላይ መገደላቸውን መንግስት ማስታውቁ አይዘነጋም። የጀርመን ድምጽም ቀድሞ ይህንን መዘገቡ ይታወሳል።

የትህነግ ሃይሎች በደረሱባቸው አካባቢዎችም ጋዝ አርከፍክፈው ንጹሃንን ማቃጠላቸውን የኢፕድ ዘጋቢዎች በስፍራው ተገኝተው ዘግበዋል። አሸባሪው ቡድን በደሴ እና አካባቢው ሽብር ለመፍጠር፡ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በማድረስ ውዥንብር ለመፍጠር አቅዶ የተነሳ ቢሆንም ይሄው እቅዱ ሰራዊቱ እና የአካባቢው ህዝብ ባደረገው ርብርብ ሳይሳካ ቀርቶአል። ህዝቡና የአካባቢው ወጣቶች በግንባር ከመሰለፍ ጀምሮ ጸጉረ ልውጦችን አድነው በመያዝ አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ እንደሆነ ዘጋቢዎቻቸን በተከታታይ መረጃ እያደረሱን ይገኛሉ።

አየር ሃይል ድጋፍ ለመስጠት የሚመጣን ሃይል እየተከተለ ከመኪና ሳይወርድ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በሁዋላ መከላከያ “የወገን ኃይል ፣ የውጊያ ሂሳብ የሚወራረደው ባሰለፈው ሃይል ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚቀር ኃይልም ጭምር መሆኑን አውቆ… የጠላት ኃይል ቀጣይ ጦርነትን ሊሸከም በማይችልበት ሁኔታ እየደመሰሰው ይገኛል። ይህ የጠላት ፍላጎት በከሃዲ መሪዎቹ ቀንም ጭምር ቆርጠው ከዚህ እንገባለን፤ እንዲህ እናደርጋለን ያሉትን ፍላጎት ሠራዊታችን በከፍተኛ ተጋድሎ እያመከነው ይገኛል” ማለቱ አይዘነጋም።

በተመሳሳይ በአፋር ጭፍራ አድርጎ የኢትዮ ጅቡቲን መንገድ ለመያዝ የተንቀሳቀሰው የጁንታው ሰራዊት በአየር ሀይላል ከተሽከርካሪ ሳይወርድ መመታቱ ተመልክቷል። የደረሰበት ሰብዓዊ ቀውስ በአሃዝ ተደግፎ ባይገለጽም የጉዳቱ መጠን ከባድ ስለመሆኑ ጥቃቱን ተከትሎ የሚወጡ ምስሎች ያሳያሉ።

የጀርመን ድምጽ ዘጋቢ በመጨረሻው የአየር ጥቃት የሞቱ ሰላማዊ ዜጎች ስለመኖራቸው ምንም እንዳልሰማና፣ ወደ ሆስፒታል የሚሄድ ቁስለኛ እንዳላየ / ሆስፒታል የመጣ ቁስለኛ አለመኖሩን/ አመልክቷል። በዚሁ ዘገባው የመቀሌ ዩኒዘርስቲ መመታቱን አልተናገረም አቅራቢያ ሲል ነው እዛው መቀለ ሆኖ ያስታወቀው። አክሎም እንዳለው በመቀለ ሕዝብ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደሚፈልግ በስፋት እንደሚገልጹለት አመልክቷል።

በሌላ በኩል አቶ ጌታቸው በሳምንቱ መጀመሪያ ሃይቅን አካባቢውን እንደያዙና ወደ ኮምቦላቻ በመቃረብ ማረፊያቸው ደሴ እንደሆነ ከግንባር ወታደራዊ ክንፍ እንደነገራቸው ገልጸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም። እስካሁን እንዳሉት የሆነ ነገር ባይኖርም በድጋሚ በቀናት ውስጥ የኢትዮጵያን መንግስት እንደሚጥሉ ለራሳቸው ሚዲያ አመልክተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በህዝብ የማይደገፍ፣ ሕዝብ የጠላውና የማይፈልገው የአንድ አካባቢ ነጻ አውጪ ድርጅት ሆኖ ሳለ ለምን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት እንደሚጓጓ ግልጽ አይደለም። የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦርናጌ ትህነግ ምን እንደሚፈልግ በስልጣን ላይ እያሉም ሆነ አሁን እንደማይገባቸው ጠይቀው ሰሞኑንንየሳፉትን የሚያስታውሱ፣ ትህነግ የትግራይ ልጆችን አስታጥቆ በምን ምክንያት አፋርን እንደሚወር፣ ለምን ድፍን አማራን እንደሚያጠቃና ምን እንደሚፈልግ በይፋ አላስታወቀም።

መንግስት መሆን፣ መገንጠል፣ ኤርትራን ወሮ መያዝ፣ ወይስ ከኢትዮጵያ ጋር መቆየት? ለሚሉት ጥያቄዎች በግልጽ መልስ የማይሰጠው የትግራይ ወራሪ ሃይል የድንበርና የማንነት ችግር አለኝ በሚልባቸው አካባቢዎች በህጋዊ መንገድ፣ ራሱ በቀረጸው ህገ መንግስት አማካይነት መፍትሄ ለማግኘት ከመስራት ይልቅ የትግራይን ሕዝብ ዙሪያውን ለምን ጠላት እንደሚያፈራለት እስካሁን ማስረዳት የቻለ አካል የለም።

ዶክተር ደብረጽዮን ” የትግራይ ህዝብ ሁሉም ወታደር ነው” ካሉ በሁዋላ በስሜት ” እንደ አባቶቻቸው እናጥፋቸዋለን” ማለታቸው አይዘነጋም። በተመሳሳይ ትናንት ከተደጋጋሚ የአየር ጥቃት በሁዋላ ” የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃቱን ያስቁም” የሚል ጥሪ ተሰምቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚንከባከበውን የአገር መከላከያ “ጠላት” በሚል ሰይሞ ከፍተኛ ቁጥር እንደገደለ ያስታወቀው መግለጫ መልሶ ” የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃቱን አስቁም” ሲል ይጠይቃል።

ሲኦል ድረስ ሄዶም ቢሆን ኢትዮጵያን እንደሚያፈርስ፣ በአማራ ላይ ሂሳብ እንደሚያወራርድ በገሃድ ያስታወቀው፣ እንደ አባቶቻቸው እንጨርሳቸዋለን … የሚለው ትህነግ ለየትኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪውን እንዳስተላለፈ በግልጽ አላስቀመጠም። ወይም “ኢትዮጵያ” የትኛዋን አገር እንደሆነ አላብራራም። ከክልሉ ወጥቶ ወረራ በማካሄድ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ፣ እየዘረፈና አገር እያወደመ ያለ ሃይል ሲመታ ” ተነካሁ” እያለ የሚያሰማው ድምጽ ለበርካቶች እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው በማህበራዊ ገጾች በብዛት እየተዘዋወረ ነው።

በትግራይ ሰብአዊ ቀውሱና የረሃብ መስፋፋት እጅግ ልብ የሚነካና ባስቸኳይ መላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። በአማራ ክልል በተለይ በዋግ ኽምራ፣ በአፋርና ድፍን ደቡብ ወሎ ቀውሱ ተመሳሳይ ነው። መፍትሄውም ጦርነት ሳይሆን ለዜጎች ሲባል የፖለቲካ ቁማርን አቁሞ ሰብአዊ ድጋፍ ላይ መረበባረብ ብቻ እንደሆነ ነገሮችን በስክነት የሚያዩ እየለፍለፉ ነው።

Exit mobile version