Site icon ETHIO12.COM

በአዲስ አበባ የተዘረፈ መሬት የማደን ዘመቻ ሊጀመር ነው

በመዲናዋ ያለ አግባብ የተወረሱና በግለሰብ የተዘረፉ የመሬት ይዞታዎችን ወደ መንግሥት ለመመለስ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጀማል አልዩ እንደገለጹት፤ ያለ አግባብ የተወረሱና በግለሰብ የተዘረፉ ይዞታዎችን ወደ መንግሥት የመመለስ ሥራ ይሠራል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግም ከፍትህና ከጸጥታ አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ውስጥ ችግር አለባቸው ተብለው ከተለዩ ተቋማት መካከል አንዱ መሬት ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በመዲናዋ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ዘረፋ፣ የአሠራር ብልሹነትና ደካማ የአስተዳደር ችግር በስፋት ይስተዋላል። ይህን ችግር ለማስተካከል የአደረጃጀት ለውጥ ከማድረግ ጀምሮ ዘርፉን በአዲስ የማደራጀት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። እንዲሁም በቀናና በአገልጋይነት መንፈስ ህዝብን የሚያገለግል አመራር የሚያስፈልግ በመሆኑ በማዕከልና በቢሮ ደረጃ የአመራር ለውጥ ተደርጓል። በቀጣይም እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ እንደሚወርድ ጠቁመዋል።

አንድን ተቋም ለመለወጥ የአደረጃጀት ለውጥ መደረግ አለበት ያሉት አቶ ጀማል፤ የመሬት አደረጃጀት በአዲስ መልኩ እየታየ ነው። ከዚህ በፊት የመሬት አስተዳደርን የሚመለከት ተቋም በዝቶ ተገልጋዩን ከቢሮ ቢሮ እንዲመለላስ በማድረስ የማሰቃየትና የማንገላታት ሥራ ሲሠራ ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍ አገልግሎቶች በተጀመሩበት ዳይሬክቶሬት እንዲያልቁ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ለስርቆት እንዲመች ሲባል እስከ ወረዳ የወረዱ መሬትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማስተካከል ማንኛውም ሰዉ እየወሰነ መሬት የሚተላለፍበት አግባብ እንዲቆም ተደርጓል። በካቢኔ ሲወሰን ብቻ እንዲተላለፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version