Site icon ETHIO12.COM

የአሸባሪውን አጀንዳ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በማጥራት ሂደት ንጹሃን ሰለባ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው

“የአሸባሪውን ህወሃት አጀንዳ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በማጥራት ሂደት ንጹሃን ትግራዋዮች ሰለባ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው” ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ ኢትዮጵያ የተደቀነባት የደህንነት ፈተና የመነጨው ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን አገር ለማፍረስና ለማዳከም አልመው ከሚሰሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎች መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ አጭበርባሪ ተዋናዮች ግባቸውን ይፋ አድርገው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያን መንግስት በመጣል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግስት ለማስቀመጥ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

“የዓለም ዓቀፍ አጋሮቻች ይህንን ተረድተው የህዝብ ምርጫ የሆነውን የኢትዮጵያ መንግስት መደገፍና ከፋፋይ አጀንዳ ካለው አሸባሪው ህወሃት በተቃራኒ ሊቆሙ ይገባል” ብለዋል።

የአገሪቱንና የመላ ዜጎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ መንግስት ያለእረፍት እየሰራ እንደመገኝ የጠሱት ዶክተር አብርሃም፤ “በአገራችን ውስጥ ሆነው ለአሸባሪው ህወሃት የሚሰሩ ሃይሎች አሉ” ብለዋል።

እነዚህ ሃይሎች ምናልባትም ንጹሐን ትግራዋዮችን በመክሰስ የአሸባሪውን አጀንዳ አስርገው ለማስገባት ሽፋን እያደረጉት እንደሆነም ገልጸዋል።

ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎች ተዋናዮች እንዳሉ ጠቁመው፤ የአገሪቱን ቀውስ ለማባባስ የተቻላቸውን እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታትና እነዚህን ተዋናዮች ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመዋል።

ኮሚቴው በፌዴራል ፖሊስና በሌሎች አጋር ተቋማት የሚወሰደው እርምጃ ስህተት እንዳያጋጥመው የሚያስችል እንደሆነም አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ንጹሀን ትግራዋዮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመጠበቅ ከትግራይ ተወላጆች ቡድን ጋር በቅርበት በመስራት ሂደቱን የመመርመርና የመገምገም ስራ እየተራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህ ፈታኝ በሆነ ወቅት በሚሰሩ ስራዎች አንዳንድ ስህተቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ስህተት እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

“አንድነታችን ጥንካሬያችን ነው” ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ “ለሉዓላዊነትና ለሰላም በምናደርገው ትግል የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቀን እናስቀጥላለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ላይ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

-አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

Ena

Exit mobile version