Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ ክልል የተሳካ ኦፕሬሽን አካሂዶ የሰዓት እላፊ ገደብ ማንሳቱን አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል በዜጎችና ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የምሽት እንቅስቃሴ ገደብ ለጊዜው መነሳቱን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዱኛ አሕመድ አስታወቁ፡፡ ክልሉ በምዕራብ ሸዋ ብቻ በልዩ ኦፕሬሽን 345 የሸኔ ታጣቂዎችን መሪዎቻቸውን መምታቱን፣ በርካታ ማቁሰሉን፣ ቁጥራቸው ያልተገለጸ መማረኩን ተገልጿል። አምቦ ወዴሳ የቀበሌ ሚሊሻ የነበረ ሰላማዊ ሰው በሸኔ ታጣቂዎች መገደሉና በጅባት ጫካ ሆነው ህዝቡን የሚያስቸግሩ እንደነበር ነዋሪዎች አማረው ነበር።

ከህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 11:30 ዜጎች እና ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ መቆየቱ ይታወሳል፡፡እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጓ፥ የክልሉን እና አገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይጎዳ ከግምት በማስገባት ይህ ውሳኔ ዳግም ተላልፏል ብለዋል።

በቀጣይ ሁኔታዎች እየታዩ አዋጁ እንደገና በመላው ክልሉ እንዲሁም እንደየ አከባቢዎች ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡የእንቅስቃሴ ገደቡ ለጊዜው ቢነሳም÷ አስፈላጊው ፍተሻ በተለያዩ የፀጥታ አካላት እና ህዝባዊ አደረጃጀት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

ከጥቅምት 2 እስከ ህዳር 8/ 2014 ዓ.ም በፌዴራል ፖሊስ፣ በኦሮሚያ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ በጋራ በተካሄደው ኦፕሬሽን በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት መደምሰሳቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልና ከሚሊሺያ አባላት ጋር በመቀናጀት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ባካሄደው የማጥቃት ዘመቻ በርካታ የሸኔ አባላት መደምሰሳቸውንና አስር ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፀው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሸባሪዎቹ በወቅቱ ሲጠቀሙበት የነበረ በርካታ ገንዘብም ተይዟል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት ጁንታ ቡድን ተላላኪ የሆነው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጮመን ወረዳ በፈጫሰ፣ አየለ፣ ችንቦና በመሳሰሉት ቀበሌዎች የህዝብ ንብረቶችን በማውደም፣ የንፁሃን ዜጎችን ህይወት በማጥፋትና መንገድ በመዝጋት ህብረተሰቡን ለእንግልትና ስቃይ መዳረጉ ታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ሀይሉ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት አሸባሪ ቡድኑ አረመኔያዊ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ የተሸሸገበት ሥፍራ በመድረስ በፀጥታ ሀይሉ የተቀናጀ እርምጃ እንደተወሰደበት ተገልጿል፡፡ በጮመን ወረዳ ገበቴ ከተማ አስር የሸኔ ተባባሪ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡

ዜናው ከተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎችና ከመንግስት ኮሙኒኬሽን የተወሰደ ነው።


Exit mobile version