Site icon ETHIO12.COM

“እየተበተነ ነው” የተባለውን የትህነግ ወራሪ አስመልክቶ ለሕዝብ አስቸኳይ ትዕዛዝ ተላለፈ፤ በርካታ ከተሞች ነጻ ወጥተዋል

በሙሉ ሃይሉ በቅንጅት ማጥቃት እንደተጀመረ ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት ጥቃቱን መቋቋም ተስኖት እየተበተነ ያለው የትግራይ ነጻ አጪ ግንባር ሃይል ወደ ዝርፊያና ከተማ ማውደም እንዳይዛወር ሕዝብ ተደራጅቶ የማጽዳትና ንብረቱን የመጠበቅ እንዲሁም ላልሰማ ሁሉ ይህን መረጃ በማደረስ ለተግባራዊነቱ እርብርብ እንዲያደርግ ታዘዘ።

“መንግሥት በህልውና ዘመቻው ወደ ተሟላ የማጥቃት ዘመቻ መግባቱ ይታወሳል” በማለት ትዕዛዙን ይፋ ያደረገው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ “የወገን ጦርን የማጥቃት ክንድ መቋቋም ያቃተው ጠላት፣ አውድሞና ዘርፎ ወደ ኋላ ለመፈርጠጥ እየሞከረ መሆኑ ታውቋል” ብሏል። አክሎም “ስለዚህም በተለይም በግንባርና በተወረሩ አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ የሚከተለውን ይፈጽም” ሲል አዟል።

1. አሸባሪው ኃይል ንብረቶችን አውድሞና ዘርፎ እንዳይሄድ በየአካባቢው በንቃት እንዲጠብቅ፣

2. የሚፈረጥጠው ጠላት እንዳያመልጥ እጅ እንዲሰጥ እንዲያደርግና ለህግ እንዲያቀርብ፣

3. ጠላት በምንም መንገድ ዘርፎና አውድሞ እንዳይወጣ ለመከላከያና ለጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ፣

4. በሁሉም የደጀን ሥራዎች ሕዝቡ ሠራዊቱን እየተከተለ በቻለው ሁሉ እንዲያግዝ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል።

“በወረራ ወደ ተያዙ አካባቢዎች መረጃ የማድረስ ዕድሉ ያላችሁ ዜጎች በሙሉ ይህ መረጃ በዚያ ለሚገኙ ወገኖቻችን እንዲደርስ በማድረግ ሕዝብና ንብረት የማዳን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡም ጥሪያችንን እናቀርባለን” ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አደራና ሃላፊነትን ለሕዝብ ሰጥቷል።

ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ በንቃት አካባቢውን በመጠበቅ እና ጠላት እንዳያመልጥ ታጥቆ እጅ እንዲሰጥ ማድረግ፣ እምቢ ካለም እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም ንብረት እንዳያወድም ለሚመለከተው የፀጥታ አካል መረጃ እንዲያቀብል ተጠይቋል።

በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ ሠራዊቱን ከኋላ በመከተል በሁሉም የደጀን ሥራዎች እንዲያግዝ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል ብሏል መግለጫው።

ሰብዓዊ እርዳታዎችን በተመለከተ በአማራ ክልል ጥቃት ለደረሰባቸው እና ወደ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች ባለፉት 3 ቀናት ብቻ 265 ሺህ 291 ኩንታል ምግብ እንዲሁም በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ለ76 ሺህ ዜጎች ከባለፈው ወር ወዲህ ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ወደ መቀሌ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ከቀናት በፊት መቀጠሉን እና ባለፉት 3 ቀናት ውስጥ 2 በረራዎች ወደ መቀሌ መደረጉን እንዲሁም በአፋር ሰመራ በኩልም 83 ድጋፍ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች መላካቸውንም የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ገልጸዋል።

Exit mobile version