Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ዳግም ‘ፈተና’ እንዳይሆን እየተደረገ ነው፤ በሺህ የሚቆጠሩ እጅ ሰጡ፤ አምስት ከተሞች ነጻ ወጡ

“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” የተሰኘው የኢትዮያ የጸጥታ ሃይሎች ጥምረት በጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ አብይ አሕመድ እየተመራ በማካሄድ ላይ ያለው የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ መሆኑንን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ። ሕዝብ ምን ማድረግ እንዳለበት መመሪያም ሰጥቷል።

“ትህነግ “የአማራ ተስፋፊ ኃይሎች በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በጋሸና፣ በታች ጋይንት፣ በጃማ፣ በወረኢሉ፣ በመሀል ሜዳ፣ በሸዋሮቢት እና በደብረሲና አካባቢዎች የሚያደርጉት መስፋፋት … ” በሚል የከተሞቹን ነጻ መውጣትና የጠቀሳቸው አካባቢዎች ሁሉ የአማራ ክልል መሆናቸውን እያወቀ ግልጽ ያልሆነ መልስ እያሰራቸ ነው።

በየአቅጣጫው ተከቦ መውጪያ ያጣው የትህነግ ወራሪ፣ ዘራፊና አውዳሚ ሃይል በሺህ የሚቆጠሩ እጃቸውን እየሰጡ መሆኑንን ያስታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ፣ በሸዋ ግንባር የቀወት ወረዳ፣ ለምለም አምባ፣ ጀውሐ፣ ሰንበቴ፣ አጣየ እና ካራ ቆሬ ከተሞችና አካባቢዎች ከወራሪው ኃይል ነጻ መውጣታቸውን፣ በጋሸናና በወረ ኢሉ ግንባር ነጻ የወጡ ስፋራዎችን ዘርዝሮ ” በየጥሻው የተበተነውን የአሸባሪ ሃይል ተደራጅታቹህ ማርኩ፣ ማርካችሁ ለሚመለከተው አስረክቡ ” ሲል አዟል።

የቀድሞ ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ህዝባዊ ማዕበል በማፍለስ የነደፉት ያረጀ የጦር ስልት ” በአፍሪካ ምርጡ ስታራቴጂስት” በሚል እንዳስወደሳቸው ቢቢሲና ሌሎች የውጭ ሚዲያዎች በስፋት ዘግበውላቸው ነበር። በወቅቱ ” ጠላት ወደ እኛ በዝለቀ ቁጥር መውጪያ እያጣ እንደሚሄድ አለማሰባቸው ያስገርማል” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መናገራቸው አይዘነጋም።

የመልሶ ማጥቃቱ ሃይል እስኪደራጅና የከተተው ሃይል እስኪሳለጥ ዘግይቶ በሳቸው መሪነት ሲጀመር የያዘውን ቦታ ሁሉ እየለቀቀ የሚሸሸውና የተከበበው ሃይል ችግር ሲገጥመው እንዴት ሊያመልጥ እንደሚችል ሳድቃን በተደነቁበት ስትራቴጂያቸው ያካቱ አያካቱ እነቢቢሲ አላስታወቁም። ይልቁኑም ትህነግ ” ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጊአያለሁ” በማለት አመልክቷል። ስልታዊ ማፈግፈግ ሲያደረግ የተከበቡትን በሙሉ አስለቅቆ ስለመሆኑ ለደጋፊዎቹም ሆነ ለምዕራብ ሚዲያዎች ያለው ነገር የለም። አቶ ጌታቸው ዛሬ ” በሁሉም ግንባር ውጤታማ ምላሽ እየሰጠን ነው” ሲሉ በቲወተር ገጻቸው ጽፈዋል። ድርጅታቸው ደግሞ ከሁለት ቀን በፊት ለተመድ፣ አሜሪካና አውሮፓ አገራት የኢትዮጵያ መከላከያ ወደ መቀለ እንዳይገባ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መተየቃቸውን፣ ለኢራን፣ቱርክ፣ ዩክሬንና ሩስያ “እባካችሁን መሳሪያ አትሽጡ” የሚል ተማልዶ ማቅረቡን አልጀዚራ መዘገቡ ይታወሳል። ለዚህም ይመስላል አስቸኳይ አዋጅ ዕዝ ” በግንባር የፈረሰውና መውጪያ ያጣው አሸባሪ የሃሰት መረጃ ያሰራጫል” ሲል በመግለጫው የጠቆመው
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ የተሰጠ መግለጫ።

የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ሕወሐት ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ነው።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት በሚያካሄዱት ‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት› ወደ ተወረሩት አካባቢዎች በጥልቀት በመግባት፣ አሸባሪው ሕወሐት ትጥቁን፣ ስንቁን፣ ኃይሉንና ጀሌውን እንዲሁም የዘረፈው ንብረት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገ ይገኛል፡፡ እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውንም እየደመሰሰው ይገኛል፡፡

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በተደረገው ኦፕሬሽን በሸዋ ግንባር የቀወት ወረዳ፣ ለምለም አምባ፣ ጀውሐ፣ ሰንበቴ፣ አጣየ እና ካራ ቆሬ ከተሞችና አካባቢዎች ከወራሪው ኃይል ነጻ ወጥተዋል፡፡ በጋሸና ግንባር ደግሞ ኮን እና ዳውንት ሙሉ በሙሉ ከአሸባሪው ጸድተዋል፡፡ በወረኢሉ ግንባር ልጓማ ከተማ ነጻ ወጥታለች፡፡ በተወረሩት አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት ባካሄዱት ኦፕሬሽን በሺዎች የሚቆጠሩ የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌዎች እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የየአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ በየጢሻው የገባውን የአሸባሪ የሕወሐት ጀሌ እጁን በሰላም እንዲሰጥ እያደረጋችሁ ያላችሁትን ጥረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ መንግሥት ያሳስባል፡፡ ኅብረተሰቡም በየአካባቢው የተበተነውን የአሸባሪው የሕወሐት ጀሌ ተደራጅቶ በመማረክ፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያውን እንዲታጠቅ፣ የቡድንና ሌሎች መሣሪያዎችን ደግሞ ለጸጥታ አካላት እንዲያስረክብ በድጋሚ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ ምርኮኛን መከባከብ የጀግንነት ባህላችን አንድ አካል በመሆኑ ማኅበረሰቡ ምርኮኞችን ለጸጥታ አካላት እንዲያስረክብ መንግሥት ጥሪ ያደርጋል፡፡

አሸባሪው ሕወሐት እየተሸነፈ በመሆኑ በግንባር ያጣውን ድል በሐሰት መረጃ ለመሸፈን እየጣረ ነው፡፡ አሸባሪው ሕወሐት የኢትዮጵያ ልጆችን ብርቱ ክንድ መቋቋም አቅቶት ሲፍረከረክ፣ የአሸባሪው አመራሮች መሸነፋቸውን ላለማመንና ወጣቶችን ውጤት በሌለው ጦርነት አሁንም ለመማገድ በማሰብ፣ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርገናል በማለት ራሱንና ተስፈኛ ጋላቢዎቹን በማጽናናት ላይ ይገኛል፡፡ አሸባሪው ሕወሐት ከዚህ በኋላ ለወረራ የገቡ ጀሌዎቹን የሚያድንበት ዐቅም የለውም፡፡ ወደተወረሩ አካባቢዎች የገባው የአሸባሪው ሕወሐት ጀሌ ሁሉም የመውጫ በሮች ተዘግተውበታል፡፡ በመሆኑም ወራሪው ኃይል በከንቱ ያሰለፋችሁ ወጣቶች ከዚህ በኋላ ማምለጫ እንደሌላችሁ ተገንዝባችሁ፣ እጃችሁን ለጸጥታ አካላት በመስጠት፣ ራሳችሁን እንድታድኑ መንግሥት ያሳስባል፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ነጻ ያልወጡ አካባቢዎችን በተሟላ መልኩ ነጻ ለማውጣት በተጋድሎ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ሁላችን ተባብረን አሸባሪው ኃይል ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመከላከያ ኃይላችንን በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በትጥቅ ዐቅም አጠናክረን በማንኛውም ወገን የሚታፈርና የሚከበር መከላከያ ኃይል መገንባት ይገባናል፡፡ መከላከያ ኃይላችንን በተሻለ ሁኔታ ለመገንባትም ሕዝቡ የጸጥታ አካላትን ለመደገፍ የጀመረውን ርብርብ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ወጣቶችም የመከላከያ ሠራዊቱን በብዛትና በዓይነት በመቀላቀል ሀገራቸው መቼምና በማንም የማትደፈር እንዲያደርጉ ታሪካዊ አደራ አለባቸው፡፡

አሸባሪው ሕወሐት ለሰው ልጅ ኑሮና ለሰብአዊ መብት የማይጨነቅ፤ የዕድገትና ለሥልጣኔ ፀር የሆነ እኩይ ኃይል መሆኑን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በገሐድ አሳይቷል፡፡ ማኅበራዊ ተቋማትን አፈራርሶና አውድሞ፣ የግለሰቦችን ንብረት ዘርፎና አጥፍቶ፣ የየአካባቢውን ነዋሪዎች ረሽኖ፣ ሴቶችን ደፍሮና በሕጻናት ላይ አሰቃቂ ጉዳት አድርሶ በሰው ልጅ ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ ከባድ ወንጀል ፈጽሟል፡፡ የሃይማኖት ቦታዎችን አርክሷል፤ አውድሟል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን አቃጥሏል፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን አፈራርሷል፡፡ ለዚህም ነው አሸባሪው ሕወሐት የትግራይን ሕዝብ አይወክልም የምንለው፡፡ በመሆኑም ይሄን የአሸባሪው ሕወሐት የጥፋት ተግባር ለሰዎች መብት የሚታገሉ ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ሕወሐት ዳግም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
ድላችንን የምናስከብረው በተባበረ ክንዳችን ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ

Exit mobile version