Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ መሳሪያ ደግኖ የዕርዳታ ዕህል መዘረፉን ፋኦ አስታወቀ፤ እርዳታም አቋረጠ

በተደጋጋሚ የዕርዳታ እህል ከተረጂዎች ጉሮሮ እየዘረፈ እንደሚያግዝ፣ ያጋዘውንንና የዘረፈውን እህልና አልሚ ምግብ ለጦር ተግባር እንደሚተቀምበት በማስረጃ ሲከሰስ የነበረው የትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን፣ ከሚያስተዳድረው ክልል ወጥቶ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎችና ከተሞች የግል. የመንግስትና የእርዳታ ድርጅት ሳይለይ ዘርፊያ መፈጸሙ በዓለም ዓቀፍ ተቋም መጋለጥ ጀምሯል።

ያላፈው ቢቀር መንግስት ትህነግ ከ1000 በላይ ከባድ መኪኖችን እንዳልመለሰ ሲጠቅስና ድርጅቱ ምንም ነገር እንዲያደረግ የተፈቀደለት በሚመስል ደረጃ አገር ሲያወድም፣ ንጹሃንን ሲጨፈጭፍና አስገድዶ ሲደፍር ዓለም ዝም ማለቱ አስገራሚ እንደሆነ በተገለጸበት ማግስት የዓለም የምግብ ድርጅት “ትህነግ ከሁለት ከተሞች ያከማቸሁትን እህል ዘረፈኝ” ማለቱ ተሰምቷል። ሰራተኞቹን በመሳሪያ አስፈራቶ አልሚ ምግብና እህል ከሁለት ከተሞች ዘርፎ ማጋዙን ድርጅቱ ቢያስታውቅም እንደ ጥፋቱ ውግዘት አልደረሰበትም። ቢቢሲ የሚከተለውን ዘግቧል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል በደሴና በኮምቦልቻ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው በአካባቢዎቹ የምግብ እርዳታ ማቋረጡን አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የእርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹ በአማጺያኑ በተዘረፉበት ወቅት በስፍራው በነበሩ ሠራተኞቹ መሳሪያ ተደግኖባቸው እንደነበረ አመልክተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደገለጸው በመጋዘኖቹ ላይ በአማጺያኑ በተፈጸመው ዝርፊያ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ከሁለቱ ከተሞች ተወስደውበታል። በስፍራዎቹ የነበሩ ሠራተኞቹም በጦር መሳሪያ ጭምር ጫናና ማስፈራሪያ ስለተደረሰባቸው ይህንን ዝርፊያ ለመከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውም ተገልጿል።

ይህ ዝርፊያ በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ በሆነበት በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግርና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን የበለጠ እንደሚያባብሰው ድርጅቱ ተናግሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ጨምሮም የመንግሥት ወታደሮች ሦስት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎችን ለራሳቸው አገልግሎት ተጠቅመዋል ሲል ከሷል።

ለአንድ ወር ያህል በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተመራው በክልልና በፌደራል ሠራዊት ጥምር ኃይል በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከአማጺያኑ ነጻ መውጣታቸው ይታወሳል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢትዮጵያ ሠራዊት በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ ባካሄደቻው ዘመቻዎች ቀደም ሲል በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ በርካታ ስፍራዎችን መልሶ በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን ከአንድ ሳምንት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብሎ ነበር።

የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየው በአማራ ክልል መሆኑን ድርጅቱ አመልክቶ፤ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር የተሰበሰቡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በሦስቱ ክልሎች ከሚገኙ ሕጻናት መካከል ከ16 እስከ 18 በመቶ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ነፍሰ ጡር ከሆኑ እና ከሚያጠቡ እናቶች መካከል 50 በመቶ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው መለየቱን እና ይህም የመንግሥታቱን ድርጅት በእጅጉ እንዳሰሰበው አመልክቷል።

በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ለሚያቀርበው ድጋፍ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት እንዳጋጠመው ገልጿል።

በዚህም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ድጋፎች ለሚደረግላቸው 12 ሚሊዮን ሰዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ የ579 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ጉድለት አጋጥሞታል።

ይህም በሰሜን ኢትዮጵያ ለ3.7 ሚሊዮን ሰዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአስቸኳይ ለሚያቀርባቸው የምግብና የአልሚ ምግቦች የሚውለውን 316 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጭምር ቢቢሲ አማርኛ ድርጅቱን ጠቅሶ ዘግቧል።

በዘረፋው ምክንያት ዕርዳታ አቁሞ እንደነበር ያስታወቀው የዓለም የምግብድርጅት ሁኔታዎችን ባስቸኳይ አስተካክሎ «በኮምቦልቻና በደሴ ምግብ ማከፋፈሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

Exit mobile version