Site icon ETHIO12.COM

የአብን አመራሮች “ህግና ስርዓት የማይከበር ከሆነ ኢትዮጵያ ትግራይን ስለመግፋት ማሰብ አለባት”

የአናሳ አምባገነን ስርዓት መስርቶ የኖረው ትሀንግ – በልክህ መተዳደር አለብህ፣ በልክህ መኖር አለብህ ነው የተባለው። በልኩ መተዳደር ያልለመደና በልኩ መተዳደር ስለማይችል፤ በሙስናና በተለያዩ ወንጀሎች የገነገን ፣ የተራቆተ መነሻ ያለውና ሃሳብ የሌለው ድርጅት ነው። ይህ ነው የሚባል ጥንካሬ የለውም። በልዩነት ውስጥ እየተሹለከለከና ማህበረሰብ እርስ በርስ እንዳይተባበር አድርጎ የኖረና በዚህ ስልት አራት ኪሎ ለመግባት ሞክሮ ሙሉ በሙሉ ሃሳቡ የተቀለበሰበት ድርጅት ነው …..

ሰሞኑንን ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ያለውን የትግራይ ጉዳይ የአብን አመራሮች ይፋ አድርገዋል። ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከንቲባ በግልጽ ” መገንጠል ከፈለጉ ማን ከለከለ” ማለታቸውን ተከትሎ የአብን አመራሮች በአማራጭና በአመክንዮ አጅበው “ካሁን በኋላ ወደ ሥርዓትና ወደ ፍትሕ የማይመጡ ከሆነ ትግራይን ስለመገንጠል ነው መወራት ያለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።

ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ብሎ የሰየመው ቡድን እንደ ስሙ ትግራይን ለመገንጠል ሁሉም አማራጮች በጁ ላይ ላለፉት 28 ዓመታት የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አላደረገውም። አሁንም ከማዕከላዊ ስልጣኑ ከተነሳ በሁዋላ ይህንኑ ዓላማውን ለመተግበር አልተንቀሳቀሰም። ይልቁኑም የተሰላቹ ዜጎች ” ለምን አይገነጠሉም” እያሉ መናገር ጀምረዋል።

ሰፊ የአማራ ክልል ከወረራ ነጻ ከወጣ በሁዋላ የአብን አመራሮች አቶ ጋሻው መርሻና አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ከትናት በስቲያ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኅልውና ዘመቻውንና ቀጣይ የትህነግን አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ሃሳባቸውን አጋርተዋል። አቶ ጋሻው የሕልውና ዘመቻውን ቀደመው የተቀላቀሉ፣ አቶ ዩሱፍም ተከትለዋቸው ግንባር የከተቱ መሆናቸው ይታወሳል። አቶ ጌታቸው ረዳም በውሳኔያቸው በመበሳጨት ” የአብን ውርጋጦች” ብለው በፌስ ቡክ ገጻቸው መሳደባቸው አይዘነጋም።

የአብን አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ወራሪውን የትግራይ ኃይል “የትግሬ ወራሪ ኃይል በማለት” በትክክለኛ ስሙ መጥራቱን ጠቅሰው በቃለ ምልልሱ መጀመሪያ የአማራ ማስ ሚዲያን አመስግነዋል። እንደ ምክንያትም አድርገው ያቀረቡት ደግሞ “አንድን ቡድን በተገቢውና ትክክለኛ ስም በመስጠት መሰየም ቀዳሚው ተግባር ስለሆነ ነው” ብለዋል።

ከዚህ በማስከተል ለደረሰው አጠቃላይ ጥፋት በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን እንደሆነ ተጠይቀው አቶ ጋሻው ትህነግ እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘውም የአክሱም ባንክን በመዝረፍ ተቋቁሞ “ከአፍሪካ ትልቁ ተቋም ነኝ” እስከማለት የደረሰውን የትህነግ ዋና የገቢ ምንጭ ኤፈረት ያለውን ንብረት በመሸጥ በጦርነቱ ለወደሙ አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም መዋል እንዳለበት ሃሳብ ሰጥተዋል።  

” ስለ ትግራይ መገንጠል ለስልሳና ለሃምሳ ዓመት ስናወራና ስንሰጋ፣ ወገናዊነታችንና ማኅበራዊ ቁርኝታችን ሊናጋ ነው በሚል (ስጋት) ስንዋጅጅ፣ ስንባዝን ኖረናል። ይህ መቆም አለበት” ያሉት የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ “ካሁን በኋላ ወደ ሥርዓትና ወደ ፍትሕ የማይመጡ ከሆነ ትግራይን ስለመገንጠል ነው መወራት ያለበት” ሲሉ የአስተሳሰቡና የፖለቲካው ቅኝት ሊቀየር እንደሚገባ አመላክተዋል። ስጋት እንደማያስፈልግና ዋጋም እንደሌለው ጠቁመዋል። አቶ ዩሱፍ አያይዘውም “ትግራይ ልትገነጠል ነው” በሚል አሁን ላይ መጨነቅና ማውራት እንደማይገባ አመልክተዋል። በግልባጩ በማብራሪያና በምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግራይን ከኢትዮጵያ ስለመለየት ወይም ስለመገንጠል ሊነጋገር እንደሚገባ በይፋ አስታውቀዋል።

አቶ ዩሱፍ እንደ ፖለቲከኛና እንደ ፖለቲካ ድርጅት አመራር በይፋ ይህን ቢናገሩም፣ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታና እየደረሰ ካለው ጥፋት ጋር ተያይዞ ” ትግራይ ትገንጠል” የሚሉ ወገኖች እየተበራከቱ ነው። ” መለያየቱ ይበጃል” የሚሉ ወገኖች ” ዛሬ ላይ አብሮ የሚያኗኑር እሴት ተንጠፍትፎ አልቋል” ሲሉ ይደመጣሉ።

መገንጠል ጥሩ ባይሆንም አሁን ካለው ውጥንቅጥ አንጻር፣ የትግራይ ተወላጆችም ሚናቸውን ለይተው በግልጽ ከየትኛው ወገን እንደሚሆኑ ማስታወቅ ባልቻሉበት ሁኔታ፣ በሁሉም ወገን እየከረረ የመጣው ጥላቻና ቂም፣ ወዘተ ቀጣዩን ጊዜ አስጊ ስለሚያደርገው የፖለቲካ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ አንዳንድ ባለስልጣናትም ጭምር በቲውተር ገጾቻቸው መግለጽ ከጀመሩ ሰንብተዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ” ማን ያዛችሁ። ራሳችሁ ያዘጋጃችሁት ህገ መንግስት አለ” ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎች ቅድሚያ ወስደው ተቃውሞ ማሰማታቸው ድርጅቱ ምን እንደሚፍለግ፣ ስሙና ግብሩ መለያየቱ፣ ዲፋክቶ መንግስት መስርቻለሁ ሲል እንዳልነበርና ነጻ ትግራይን ለማቋቋም ከጫፍ መድረሱን እንዳላስታወቀ ዛሬ ” መንገዱ ክፍት ነው” ሲባል ቁጣ የተሞላው ግብረ መልስ ምስጠቱ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር።

እጅግ ምስኪንና ውብ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ቢኖሩም አሁን ላይ ጣላቻውን ዛቻው ከልክ በላይ በመጎኑ ለጊዜውም ቢሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊወሰን እንደሚገባ፣ ይህንኑ ጉዳይ ይዘው እየተነቀሳቀሱ ያሉ መኖራቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን ያታወሳል። የኢትዮጵያ መከላከያ በትግራይ ወገኖቹ ፊት የደረሰበት ጥቃት መነሻ አድርጎ የተጀመረው ጦርነት ዛሬ ዓመት ከሶስት ወር ሆኖታል። በርካታ ህይወት አልፏል።ንብረት፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወድመዋል። በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። በሚሊዮኖች ተርበዋል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ የትግራይ ሃይሎች አብዛኛውን አማራ ክልልና አፋርን ወረው አስነዋሪ ድርጊቶችን ጨምሮ ተጠቃሎ ሪፖርት ያልቀረበበት ውድመት አካሂደዋል።

የትም ይሁን የት የጤና ኬላዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ተምህርት ቤቶችና አምራች ተቋማትን ማውደም ትርጉሙ ለማንም ግልጽ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ፣ የትግራይ ሕዝብ ይህንን በገሃድ ለምን አይቃወምም የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። መነኩሴ አዛውንት ሳይቀር በመድፈር፣ በጅምላ ነጹሃን አርሶ አደሮችን መንደራቸው ድረስ በመዝለቅ መጨፍጨፍ … ማንም የሰው ልጅ ላይ ሊደርስ የማይግባው ድርጊት መፈጸሙ በየደረጃው ስሜትን እንዳበላሸ መሸሸግ አይቻልም። አቶ የሱፍ መነሻቸውን ዘርዝረው ሃሳባቸውን ሲሰጡ ያቀረቡት ” ህግና ስርዓት ማክበር ከልተቻለ” በሚል መነሻ ” ትግራይን ገንጥሎ መገላልገል” ወደሚለው ድምዳሜ መቃረባቸውን ነው ያሳዩት።

በቃለምልልሱ ማብቂያ ላይ አቶ ዩሱፍ “ የፖለቲካ ቅኝቱ ራሱ መቀየር አለበት፤ የፖለቲካ ቅኝቱ እኔ ሁሉንም ነገር ካልወሰደኩኝ ብቻ ሳይሆን አንተን ሁሉንም ነገር ካላሳጣሁህ አሸናፊ ልሆን አልችልም የሚል የተዛባ የፖለቲካ እሳቤ ስላለ ነው። ከዛሬው እንዲወሰድልኝ የምፈልገው እስከዛሬ ድረስ በአገራዊ ቅን እሳቤ፣ በማኅበራዊ ቅን እሳቤ ብዙ ነገሮችን፣ በጎነትን፣ ታሪክን፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ታሳቢ በማድረግ ስንገለገልባቸው የነበሩ አገራዊ እሴቶችን ያጎደፈ ስብስብ ነው ያጋጠመን፤ ይህንን ወደ ሕግ ማዕቀፍ ማቅረብ እንዳለ ሆኖ ግን አንድ እርምጃ ወደፊት እየተራመድን ጉዳዩ በሚመጥነው ልክ ልንቆም እንደምንችል የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ፖለቲከኛው፣ ምሑራኑ፣ ውይይት እንዲጀምር እኔ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ምን ለማለት ነው ካሁን በኋላ ስለ ትግራይ መገንጠል ለስልሳ፣ ለሃምሳ ዓመት ስናወራ፣ ስንሰጋ ወገናዊነታችን፣ ማኅበራዊ ቁርኝታችን ሊናጋ ነው በሚል (ስጋት) ስንዋጅጅ፣ ስንባዝን ኖረናል። ይህ መቆም አለበት። ካሁን በኋላ ወደ ሥርዓትና ወደ ፍትሕ የማይመጡ ከሆነ ትግራይን ስለመገንጠል ነው መወራት ያለበት፤ ስለ ትግራይ መገንጠል አይደለም አሁን ልናወራ የሚገባን”

ሙሉውን ቃለምልልስ ማዳመጥ ተገቢ ስለሆነ ለዚሁ እንዲረዳ ከዚህ በታች አስቀምጠነዋል።

Exit mobile version