Site icon ETHIO12.COM

“የፈጠራ ቅጥፈቶች ለጊዜው ቢያደናግሩም፣ እውነት የመሆን ዐቅም ግን የላቸውም”

አሸባሪው ሕወሐት የራሱ ወንጀሎች እንዳይገለጡበት አስቀድሞ ሌላውን የመወንጀል ስልቱ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ የሰሜን ዕዝን ራሱ አጥቅቶ የለኮሰው ጦርነት በሌሎች ላይ ለማላከክ እስካሁን እየዳከረ ነው፡፡ በጦርነት ያስጨረሳቸውን ወጣቶች አስከሬን በተከዜ ወንዝ ላይ ራሱ እየጣለ፣ ንጹሐን እንደተጨፈጨፉ ለማስመሰል የሠራው ድራማም በቂ ተመልካች አላገኘለትም፡፡

አንዳንድ የአሸባሪው አፈ ቀላጤዎች የሆኑ የምዕራብ ሚዲያዎችና አብረዋቸው በሰብአዊ መብት ስም የሚሠሩ ተቋማት በአማራና በአፋር ክልሎች፣ ከጦርነቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው፣ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንጹሐን ዜጎች ላይ በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ ጭና፣ አጋምሳ፣ ውጫሌ፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ ኮምቦልቻና ጋሸና በአሸባሪው ሕወሐት የተፈጸሙ ዘግናኝና አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋዎችን ማየትና መስማት አይፈልጉም፡፡ አሸባሪው ሕወሐት በረገጠባቸው አካባቢዎች ሁሉ ዛሬም ድረስ የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው፡፡

ይህ አሸባሪ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች እጅግ ዘግናኝ ወንጀልና ጭፍጨፋ በሰው ዘር ላይ ተፈጽሟል፡፡ አፈ ቀላጤዎቹ የውጭ ሚዲያዎችና ሰብአዊ መብትን እናቀነቅናለን የሚሉ ተቋማት ግን ዓይኔን ግንባር ያርገው ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ ‹በምዕራብ ትግራይ› በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል የተለመደ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ያለበት፣ ለሰሞነኛ ስብሰባ ማድመቂያ የሚውል የፈጠራ ክስ፣ በአንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች እየተራገበ ይገኛል፡፡

ይህ የፈጠራ ክስ በተመሳሳይ የይዘት ቅርጽ፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተመሳሳይ አገላለጽና አቀራረብ፣ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ሚዲያዎች መቅረቡ፣ ነገሩ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው፣ ከአንድ ቦታ ታቅዶ ለሁሉም የተሠራጨ የፈጠራ ክስ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ከመርሕና ከሞራል ውጭ የሆነውን ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ ያወግዘዋል፡፡ ለኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳው ነው፡፡ ይሄንን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለውን የዜጎችን ሰብአዊ መብት በተሟላ መልኩ ለማስፈጸም ከለውጡ ወዲህ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋም መሥርቷል፡፡

ከዚህ በፊት ተፈጥረዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡ የምርመራ ግኝቶችንና ምክረ ሐሳቦችን መሠረት አድርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ከተባሉም የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ የሰብአዊ መብት ተቋማት አማካኝነት እያጣራ፣ በፍትሕ አካላት በኩል ተገቢውን ለማድረግ አሁንም ቁርጠኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ሰው ተኮርና ለሰዎች መብትና ዕሴት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ በመሆኑ፣ የሰብአዊ መብቶች መከበር የብልጽግና ጉዟችን ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ በጀመርነው አቅጣጫ አጠናክረን እንደምንቀጥል ለሕዝባችንና ለወዳጆቻችን እናረጋግጣለን፡፡

ኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት


Exit mobile version