Site icon ETHIO12.COM

አፋር “የትግራይ ሕዝብ የትህነግን እብደት በቃ በል”ሲል ተማጸነ፤ መጋሌና አብአላ ተወረሩ

የሰላም እርምጃው ተስፋ እንዳለው በሚገለጽበት ወቅት የትህነግ ቡድን በአፋር ከሚያዋስነው ስፋራዎች ላይ ስፍራ እየቀያየረ ከባድ መሳሪያ በመጠቀም ንጽሃንን እየፈጀ መሆኑ ተገለጸ። ክልሉ ቃል በቃል ባይገልጽም መጋሌና አብአላ የተባሉ አዋሳኝ ከተሞችን የትህነግ ሃይል ወሯል። ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ” መከላከያ ለቀጣይ ዘመቻ ዝግጅቱን አጠናቆ በመተባበቅ ላይ ነው” ማለታቸው በማስታወስ መከላከያ ሊታዘዝ እንደሚችል ተጠቁሟል። ክልሉም በአካባቢው ምን ዓይነት የልዩ ሃይል እንዳልነበረ አስታውቆ “የምድር ድሮኖችን አሰማራለሁ” አስጠንቋቋል።

የአፋር ክልል መንግስት አሽባሪው ህወሓት በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል በአብአላና በመጋሌ ወረዳ የከፈተውን ውጊያ አጠናክሮ መቀጠሉን ዛሬ ሲያስታውቅ ነው ለትግራይ ሕዝብም ትሪውን ያቀረበው። ቡድኑ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ንጽሃን ዜጎችን እያሸበረ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ዛሬ ሰኞ በኪልበቲ ረሱ (ዞን) በተለያዩ ቦታዎች የክልሉን ወሰን ጥሶ በመግባት በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንፁሀንን መዳረጉዳቱን የአፋር ክልል አስታውቋል። ይሁን እንጂ የጉዳት መተኑንን አላብራራም። ድርጊቱ አሁን ብቻ ሳይሆን የመንግስት ሃይል ወደ ትግራይ የሚያደርገውን ግስጋሴ ማቆሙን ተከትሎ የተጀመረ እንደሆነ ሲገለጽ ነው የሰነበተው። የትህነግ አመራሮች በበኩላቸው ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ፣ በዚህም የተነሳ መድሃኒትና ዕርዳታ ማስገባት እንዳልተቻለ በየዕለቱ እያስታወቁ ቢሆንም፣ ይህ የሚሆነው ሆን ተብሎ የሱዳንን ኮሪዶር ለማስከፈት ጫና እንዲደረግ መሆኑ በኢትዮጵያ ወገን ምላሽ የተሰጠበት ነው። ኢትዮጵያ የሱዳንን ኮሪዶር ” ቀይ መስመር” ስትል የሰየመችውና በምንም መልኩ ለድርድር የማታቀርበው ጉዳይ እንደሆነ ደጋግማ በገሃድ ማስታወቋ አይዘነጋም።

ህወሓት በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ዘልቆ በመግባት ንፁሀን የጎዳ ቢሆንም ጥቃት እንደተፈፀመበት አስመስሎ በማቅረብ አሁንም ማደናገሪያውን እየነዛ እንደሆነ አፋር ክልል አመልክቷል። አያይዞም “የትግራይ ህዝብ የህወሓትን እብደት በቃህ ሊል ይገባል” ሲል ጥሪውን አቅርቧል። ሕዝቡ በግልፅ እየወጣ ያለውን የትህነግ ሴራውና ተንኮሉን በመረዳት፣ ከህዝብ የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለ፣ ይህንኑ በመረዳት የትግራይ ሕዝብ በአፋር ሕዝብ ላይ የሚደረገውን ትርጉም አልባ ግድያና ማሸበር መቃወም ግድ እንደሚሆንበት አስጠንቅቋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ህወሓት በምላዛትና በዳንደ በአፋር ልዩ ኃይል ጥቃት እንደፈፀመና የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት ጎሳ መሪዎች ከድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲያደርጉ ሲል ጥሪ አቅርበው እንደነበር ክልሉ አስታውሷል። ይሁን እንጂ ትህነግ ጥፋቱን ቀጥሎበታል።

ይህንንም ተከትሎ የአፋር ክልል እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ሸሪአ ፍርድ ቤት እና የሀገር ሽማግሌዎች በሰጠው ምላሽ ” በከባድ መሳሪያ በየቀኑ የንፁሀን ነፍስ እያጠፋችሁ ፣ በውሸት ተወረርን በማለት እና ሰላም ፈላጊ መስሎ መቅረብ የተለመደው ማደናገሪያችሁ ከመሆን ውጪ በፍፁም ተቀባይነት የለውም ” ብሏል።

በጠቀሱት ቦታዎች ላይ አንድም የአፋር ልዩ ሀይል እንደሌለ አስገንዝበዋል፤ የህወሓት ክስ ዓለምን በውሸት የማደናገሪያ መሆኑንን ተመልክቷል። ትህነግ “ተጠቃሁ” በሚል አቋሙ እንደጸና በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚያሰራቸው መረጃ ለመረዳት ይቻላል።

ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ቆቦ፣ አዲአርቃይ አካባቢና በተጠቀሱት የአፋር ስፍራዎች ትንኮሳ መኖሩን በመጥቀስ የአገር መከላከያ ሰራዊት ዝግጅቱን አጠናቆ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

ትህነግ የሱዳንን ኮሪዶር ለማስከፈትና በሱዳን ያለውን የሳምሪ ሃይል ለማስገባት ዕቅድ እንዳለው አቶ ጌታቸው መናገራቸው ይታወሳል። ፎሪን ፖሊሲ እሳቸውን ጠቅሶ እንዳለው ታጥቆ ሃይላቸውን ለመቀላቀል የተዘጋጀ ከሰላሳ ሺህ በላይ ታማኝ ሰራዊት በሱዳን እንዳላቸው ዘግቦ ነበር። አማራ ክልል በበኩሉ ጨዋታው የቁጥር መሆኑንን አመልክቶ የተጠቀሰውን አሃዝ እንዳታታለ አይዘነጋም። ይህ በንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያና የሱዳን አዲሱ ግንኙነት የሱዳን ኮሪዶርን ጥያቄ ወደ ምን ሊወስደው እንደሚችል በርካቶችን እያነጋገር፣ የትህነግን ሰዎች ያስጨነቀ ሆኗል።

የክልሉ ሙሉ መግለጫ

አሸባሪው ህወሀት በአፋር ውስጥ ገብቶ የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ አሁንም በኪልበቲ ረሱ /ዞን/ ጦርነት ከፍቷል!

አሸባሪው ህወሀት በአፋር ክልል ውስጥ ገብቶ የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ለማካካስ በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል በአብአላና በመጋሌ ወረዳ የከፈተውን ውጊያ አጠናክሮ ቀጥሏል። ምንም አይነት ሰብአዊነትና ርህራሄ ፈፅሞ የሌለው አሸባሪው ቡድን በንፁሀን ዜጎች ላይ ከባድ መሳሪያ በመክፈት እያሸበረ ይገኛል።

ሁሌም ከትንኮሳ አርፎ የማያውቀው የሽብር ቡድኑ ለዘመናት የቆየውን በድንበር የሚዋሰኑ የአፋር እና የትግራይ ህዝቦችን ግንኙነት ከምንም ሳይቆጥረው ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት የማይረባ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን እየጣረ ይገኛል። እያደረሰ ባለው ጥቃትም የአፋር ንፁሃን ኢላማ በማድረግ የሽብር ተግባሩን በማስፋት ላይ ነው።

በዛሬው እለት እንኳን በኪልበቲ ረሱ (ዞን) በተለያዩ ቦታዎች የአፋር ክልልን ወሰን ጥሶ በመግባት በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንፁሀንን ለጉዳት ዳርጓል።

ይሁንና ሁሌም በማጭበርበርና በውሸት ፕሮፖጋንዳ እድሜውን የሚያራዝመው ጁንታው በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ዘልቆ በመግባት ንፁሀን የጎዳ ቢሆንም ጥቃት እንደተፈፀመበት አስመስሎ በማቅረብ አሁንም ማደናገሪያውን እየነዛ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሀት በአራት ዞኖች ውስጥ በ 21 ወረዳዎች ወረራ በማካሄድ የአፋር ህዝብን በአሰቃቂ ሁኔታ ቢጨፈጭፍም፣ በብዙ ቢሊየኖች የሚገመት ሀብት ንበረት ቢያወድም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ እንዲሰደድ ቢያደርግም ለጎረቤት ትግራይ ህዝብ ሰብአዊነት ሲባል እርዳታ በአፋር አብአላ በኩል እንዲያልፍ እየተደረገ ነበር። ነገር ግን ጁንታው ለትግራይ ህዝብ እንኳን ምንም አይነት ርህራሄ እና እዝነት ባለመኖሩ በዚሁ ቀጠና ግጭት በመፍጠር አካባቢው የግጭት ቀጠና እንዲሆን እና ሰብአዊ እርዳታ እንዳያልፍ አድርጓል።

የትግራይ ህዝብም የዚህን አሸባሪው ህወሀት እብደት በቃህ ሊል ይገባል፣ በግልፅ እየወጣ ያለውን ሴራውን እና ተንኮሉን በመረዳት ከህዝብ የሚበልጥ የለምና እንደ ህዝብ ሊቃወም ግድ ይላል። በውሸት ማወናበጃው ፈፅሞ ባለመታለል ለጥቂት የቡድኑ አባላት ጥቅም ሲባል የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን መገበር አይገባቸውም።

በአፋር በተለያዩ አካባቢዎች ወረራ አካሂዶ በሁሉም ግንባሮች ሽንፈትን አስተናግዶ የወጣው አሸባሪው ህወሀት አሁንም እንደ አዲስ በኪልበቲ ረሱ (ዞን) በኩል በከፈታቸው ግንባሮች የምድር ድሮኖቹ አስፈላጊውን መከታና ማጥቃት በማካሄድ የጁንታውን እብደት የሚያመክን በመሆኑ አሸባሪው ቡድን ዘልቆ ገብቶ ለመውረር ያስገባውን ሀይሉን አስቀድሞ ሊያወጣ ይገባል!

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ጥር 16/2014

ሰመራ

Exit mobile version