Site icon ETHIO12.COM

ማንዴላ የፖሊስ ስልጠና የወሰዱበትን ማዕከል የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ስምምነት ተፈረመ

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱበትን የኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከልን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንረት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ፣ በአፍሪካ የነጻነት ትግል ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ የሚታወቁትና የአለም የሰላም አምባሳደር የኔልሰን ማንዴላ የትግል ህይወት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነውን ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱበትን ማዕከል ወደ ሙዚየምነት ለመቀየርና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በመወሰኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፖሊስ ቀደምት ታሪክ የሚዘከርበትና ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነጻነት ታሪክ ትልቅ ድርሻ እንደነበራት ማሳያ ይሆናልም ብለዋል።

ማንዴላ ፖሊሳዊ ስልጠና የወሰዱበትን ማሰልጠኛ ማዕከል የቱሪዝም መዳረሻ መደረጉ ቀጠናዊና አህጉራዊ ትስስር እንዲጠናከርና ስለአፍሪካ ጉዳዮች በጋራ እንድንወያይ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱበት ህንፃን የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ በማድረግ በአፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና እና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ሀብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ፣ የቱሪስት ፍሰቱንና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በአፍሪካዊያን የነፃነት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያን ሚናን አጉልቶ ለማሳየት ይረዳል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረትን ከሀገራችን ለማስነሳት ለሚሞክሩ ሁሉ በነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ስም ሙዚየሙ መገንባቱ ፖለቲካዊ ጠቀሜታው እንዲጎላ ያግዛልም ብለዋል ዶ/ር ሂሩት።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

Vis EPD

Exit mobile version