Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የተሳካ ሙከራ አካሄደ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሶስት ዓመታት በኋላ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ የሙከራ በረራውን ያከናወነው ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ባካሔደው የደርሶ መልስ በረራ እንደሆነም ተገልጿል።

ለሙከራ በረራውም እ.አ.አ በ2018 የቦይንግ አውሮፕላን በረራ መቆጣጠሪያ ክፍሉ ላይ በታየው የቴክኒክ ችግር ምክንያት አደጋ ከተከሰተ በኋላ የበረራ አገልግሎት እንዳይሰጡ ከታገዱት አውሮፕላኖች መካከል ቦይንግ 737 ET-AVI ET 9201 የተባለ አውሮፕላን መጠቀሙንም ጨምሮ ጠቅሷል።

በረራውም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሶ መልስ የተከናወነ ስለመሆኑም መረጃው አመላክቷል። ሙከራው የቦይንግ አውሮፕላን በቴክንክ ችግር ምክንያት ለአደጋ ተጋልጦ ለበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፍ እና ንብረት ውድመት ምክንያት ከሆነው አደጋ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው መሆኑም ተገልጿል።

እንዲህ አይነቱ የሙከራ በረራ የቦይንግ አውሮፕላን ወደ መደበኛ የበረራ አገልግሎት እንዲመለስ ለማድረግ አይን ገላጭ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል። አየር መንገዱ ከቀናት በኋላ የቦይንግ አውሮፕላኖቹን ወደ በረራ ሊመልስ ስለመሆኑ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

Exit mobile version