Site icon ETHIO12.COM

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ህወሀት 9ኛ ዙር ስህተት ከመፈፀም እንዲቆጠብ አሳሰቡ

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሸብሪው የህወሀት ቡድን 9ኛ ዙር ስህተት ከመፈፀም እንዲቆጠብ አሳሰቡ።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡና የመቆያ ጊዚያቸውን ለሸፈኑ የሰራዊት አመራርና አባላት የሜዳሊያ ሽልማትና የማእረግ እድገት ሰጥቷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የጥቁር አንበሳ ሜዳይ ተሸላሚዎቹ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ፣ የአድዋ ድል ሜዳይ ተሸላሚ የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ጄነራል ጌታቸው ጉዲና እና ሌሎች ጄነራል መኮንኖች ተገኝተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ አሸባሪው ቡድን ባለፉት ጊዜያት 8 ጊዜ ስህተት መሳሳቱን አስታውሰው ቡድኑ 9ኛ ዙር ስህተት ላለመፍጠር ቁጥብ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቡድኑ አሁንም የምእራብ ኮሪደርን አስከፍታለሁ ብሎ ማወጁን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ ይህንን እቅዱን ለመተግበር ከተንቀሳቀሰ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድና ለዚህም ተቋሙ በሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል ።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ፣ አሸባሪው ቡድን በጋሸና መስመር ያሳየውን የእብሪት ተግባር በማስተንፈስ በሰው ሃይሉ፣በማቴሪያልና በሞራል ደረጃ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረግ ተችሏል።

የሽብር ቡድኑ በቀጣናው በተደጋጋሚ ሾልኮ ለመውጣት ያደረገው ሙከራ በእዙ አመራርና አባላት ተጋድሎ መና ማስቀረት መቻሉንም ተናግረዋል።

በዕለቱ የተለያዩ ወታድራዊ ትርኢቶች የተከናወኑ ሲሆን ፣ በግዳጅ አፈፃፀማቸው የተሻለ ላስመዘገቡ ክፍሎች ፣አመራርና አባላት የሜዳይና የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል።

ወንድሜነህ አምባዬ

Exit mobile version