Site icon ETHIO12.COM

❝በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!❞ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

በወረራው ወቅት ቤተሰባቸው ያጡ አባት ያደረባቸውን ሃዘን መናገር ተስኗቸው ሲያለቅሱ

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ባስተላለፈው መልዕክት ❝በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!❞ ብሏል። ፓርቲው ከልወጡ ጀምሮ በቀድመው መዋቅር ውስጥ ባሉ ሃይሎች ሴራ እየተመረተለት ሊረጋጋና ሰላም ሊሰፍንበት አልቻለም። ከዛም አልፎ ትህነግ “ኢሳብ ኧራርዳለሁ” ብሎ ክልሉን ዱቄት በማድረግ፣ ሕዝቡን ስነልቦናውን በመንካትና ንብረቱን በማውደም በቅለላሉ ሊረሳ የማይችል እንድንጋይ ዘመን ውስጥ ከቶታል።

በዚህ ቁጭት ወረራውን እንደቀለበሱት ሕብረት ፈጥረው ይሰራሉ ሲባል አሁንም ስም በሚቀያይር ሴራ ክልሉ እየታመሰ ዳግም ጠላት ወደ አመድነት እንዲቀይረው እየተሰራ ነው። ሕዝብ ይህንን ስመሊረዳ ሩጫው ባይሳካም ዛሬ ላይ ግብግቡ ወደ ማብቂያው መድረሱ በሚነገርበት ወቅት ላይ ፓርቲው ይህን መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ለውጡ በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ከጅምሩ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገብ የጀመሩበት ኢትዮጵያውን በአጠቃላይ እና በተለይም የአማራ ህዝብ ለውጡን ደግፈው የቆሙበት ሁኔታ የሚታወስ ነው፡፡ ለለውጡ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ህዝባዊ ጥያቄዎች በተለይም የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት፣ የኢኮኖሚ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ እርምጃዎችና የተካሄዱ ሪፎርሞች፣ የማህበራዊ ልማት ማሻሻያዎች፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮችን የመለየትና የማረም፣ የፀጥታ የፍትህና የደህንነት ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሕግ ሪፎርሞች፣ የትላልቅ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ችግር ተፈቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውጥ… ወዘተ የለውጡ አበይት ትሩፋቶች የታዩባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡

በእነዚህ ትልልቅ ሀገራዊ ለውጦች ሂደት ውስጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጦር ሰብቀዋል፤ እንደሀገርም ሆነ እንደሕዝብ ወግተውናል፡፡ በሕዝብና በሀገር ላይ የተወረወሩ ጦሮች በአይነትም ሆነ በይዘት የተለያዩ ነበሩ፡፡ ከአሸባሪው ትህነግ እስከ በአምሳሉ እስከፈጠራቸው የተደራጁ ሽፍቶች ድረስ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወግተዋል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ቁሞ ቀሮች በግለሰብና በጠባብ ቡድንተኝነት ኔትወርክ ፈጥረው ብልጽግና ፓርቲን ለመናድ በሀሳብ ከመታገል ይልቅ ስም ማጥፋትን እንደትግል መሳሪያ ተጠቅመው ፓርቲውን ከውስጥ ለማፍረስ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቅዠታቸው እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ሕዝብ የሚበጀውን ያውቃልና ነፃና ገለልተኝነቱ በተመሰከረለት ምርጫ አመኔታና ይሁንታውን ለብልጽግና ሰጥቷል፡፡ ፓርቲያችን ለአምስት ዓመት ከሕዝብ የተሰጠውን ይሁንታ ተቀብሎ ብልጽግናን እንደራዕይ በማንገብ በሀገር በቀል እሳቤ እየተመራ፣ ወንድማማችነትን (ሕብረ-ብሄራዊነትን) መለያ ባህሪው በማድረግ፣ ከዋልታ ረገጥ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ይልቅ የመሀል ፖለቲካን (centrism) በማራማድ ለውጡን ብቻ ሳይሆን የተሳካ የትውልድ ሽግግርን እውን ለማድረግ የማያቋርጥ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብልጽግና ፓርቲ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራወችን እየሰራ ይገኛል። በዚህ ጉባዔ አመራርና አባሉን በሚገባ ፈትሾ በአስተሳሰብ ውግንናው ለህዝብና ለሀገር አንድነት አቅም የሆነ የጠራ አመራርና አባል ይዞ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንዲሳካም በቅድመ ጉባዔ መድረኮች ከላይ እስከ ታች ያለውን አመራርና አባሉን በግምገማዊ የስልጠና መድረኮች እያበቃና እያጠራ ይገኛል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ልክ እንደ ብአዴኑ ዘመን ጉባዔ በተቃረበ ቁጥር አንድም በውስጣችን ያሉ ቁሞቀሮች ለሥልጣናቸው በመስጋት በሌላ መልኩ ደግሞ በህልውና ዘመቻው የተሸነፉና ተስፋ የቆረጡ ትሕነግና የትሕነግ ወኪሎች ፓርቲውንና የፓርቲውን አመራሮች ከህዝብ ለመነጠልና የተለመደውን ሀገርን የማፍረስ ፕሮጀክታቸውን የጉባዔውን ወቅት ተጠቅመው ሰፊ የሞት ሽረት ትግል እያካሄዱ ነው። ለዘመቻቸው የሚያቀርቡት ምክንያት የተለያየ ይሁን እንጂ ግባቸው በሕዝብ አመኔታ ያገኘውን ብልጽግና ፓርቲን ከውስጥና ከውጭ መናድ፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡
ከነዚህም መካከል በቅርቡ በወለጋ በወገኖቻችን ላይ በከፈቱት ጥቃት የደረሰው የሞት አደጋ በሌላ መልኩ ደግሞ የአማራ ክልልን በማያቋርጥ የጥፋት አጀንዳ ህዝባችንን ማህበራዊ ረፍት ለመንሳት እያደረጉ ያሉት ጥረት ለማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው። በእነዚህ ሁሉ አልሳካ ሲል ደግሞ ጉባዔውን መሰረት ያደረጉ ውዥንብሮች እና የሐሰት ክሶችን መሰንዘር ቀጥለዋል። እነዚህኞቹ ኃይሎች በአመለካከት ደረጃ ከሕዝብና ሕዝብ አመኔታ ከጣለበት ገዥው ፓርቲ ጋር ሳይሆን ለጠላት የሚቀርቡ ናቸው፡፡

በመሰረቱ በፓርቲው የአሰራርና ህገ-ደንብ መሰረት ማንም አመራርና አባል በፓርቲው አሰራሮች ‘ግልፀኝነት ይጎድለኛል’ ካለ ማብራሪያ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ምላሽ እንዲሰጠው ለተገቢው ህጋዊ የፓርቲው የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ጥያቄውን ማቅረብም ይችላል፡፡ ነገር ግን ህጋዊውን አሰራር ተከትሎ ገና ምላሽ ባልተሰጠበት ሁኔታ የፓርቲውን ስምና አመራር በሐሰት መረጃወች ለመወንጀል መሞከር ህገወጥነት ብቻ ሳይሆን በፓርቲ ጉባዔ ሰሞን ጀግና መስሎ ለመታየት የመሞከር የከሰረ ብአዴናዊ መንገድ ነው።

በሌላ በኩል ከገንዘብ ጋር በተያያዘ በአመራሩ “ተዘረፈ” “ተከፋፈለ” ተብሎ የተጠቀሰው ገንዘብ ፍፁም መሰረተ ቢስ ውንጀላ ሲሆን በፓርቲው ወጪ የተደረገ ምንም አይነት ገንዘብ የለም፤ ይህንንም በፓርቲው በውስጥና በውጭ ኦዲተር ኦዲት የተደረገበትን ማስረጃ ማንኛውም አካል በማንኛውም ጊዜ ቀርቦ መጠየቅና ማረጋገጥ የሚችለው እውነታ ነው።

እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ በፓርቲያችን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ውስጥ የሚሰሩ አመራሮች እና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች በሌሎች ተቋማት እንዳለው ሕጋዊ አሰራር በረዥም ጊዜ የሚመለስ የብድር አገልግሎት ለአበዳሪ ተቋማት ካቀረቡ እና አበዳሪ ተቋማት መስፈርቱን አሟልተው እና የብድር ማስያዥያ (Collateral) አሲዘው ካፀደቀላቸው አመራርም ይሁን ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ብድር የሚያበድሩበት አሰራር የቆየና ለዓመታትም እየተሰራበት የመጣ ህጋዊ አሰራር ነው፡፡ ይህ ህጋዊ አሰራር ደግሞ የሚመለከተው አበዳሪ ተቋማትን እንጂ ፓርቲውን አይደለም፡፡

የሚገርመው አንዳንድ በስም የተጠቀሱ ከፍተኛ አመራሮች ጭራሽ በብድሩ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ብር እንደተከፋፈሉ ተደርጎ በሀሰት ስማቸውን ለማጥፋት ከመሞከሩ በተጨማሪ ከአበዳሪ ተቋማቱ ባረጋገጥነው መረጃ መሰረት የአበዳሪ ተቋማቱን ህጋዊ የዋስትና ስርዓት አሟልተው በተለያዩ ዓመታት የተበደሩ ጥቂት አመራሮችና ሰራተኞችም ቢሆኑ ከተቋማቱ የተበደሩት የብድር መጠን ሆን ተብሎ ስም ለማጥፋት በቀረበው መንገድ ሳይሆን አበዳሪ ተቋማቱ በአሰራራቸው መሰረት የሚፈቅዱት የብድር መጠን ነው፡፡
መሰል አሰራሮች በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ፓርቲያችያንም በሕጋዊ የአሰራር መንገድ ሰራተኞቹ የብድር ተጠቃሚ ቢሆኑ የሚደግፍ እንጂ ሚያደናቅፍበት አንዳች ምክንያት የለውም፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የብልጽግና ጉባዔ አደናቃፊዎች፣ ጉባዔውን መሰረት ያደረጉ ውዥንብሮች እና የሐሰት ክሶችን መሰንዘር መርጠዋል፡፡ ይህም ሆኖ ፓርቲያችን ውስጡን ከማጥራት በሕዝብ የተጣለበትን አመኔታ ከመወጣት ለአፍታም ቢሆን ወደኋላ አይልም፡፡

አመራራችን የአማራ ሕዝብ እንደሕዝብ፤ ክልላችን እንደክልል፤ ኢትዮጵያም እንደሀገር የተጋረጠባትን ፈተና በውል ይገዘነባል፡፡ ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር ለማረጋገጥ ርብርብ በማድረግ ላይም ይገኛል፡፡ በየደረጃው ያለው የክልላችን አመራር ሙሉ ትኩረቱ በአሸባሪውና ወራሪውን የትግራይ ኃይል የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ዳግም ወረራ እንዳይከፈት ለመመከት፣ ነፃ ያልወጡ ቀሪ የተወሰኑ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት ብሎም ጠላትን ለመቅበር በሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት ላይ አድርጓል፡፡ የተቀናጀ፣ የዕዝ ሰንሰለቱን የጠበቀ፣ ተጠያቂነት ያለበት አመራር በማረጋገጥ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡

በሂደቱ የሚያጋጥመንን የትኛውንም አይነት የሴራ ድር በጣጥሰን የምናልፈው ሕዝብን ማዕከላችን አድርገን ነው፡፡
በዚህ ሂደት በሕዝብ ጫንቃ ላይ የወደቁ፣ በትላንት ያረጀና ያፈጀ የሴራ ፖለቲካ መንገድ እየተጓዙ የሕዝብ ልጅ ከመሆን ይልቅ ሸክም የሆኑ አመራሮች ከሕዝብ ትክሻ ላይ ተራግፈው የአመለካከት ጥራት ያለው፣ የወቅቱን የትግል መድረክ በድል የሚወጣ ብቁ አመራር እንዲፈጠር ያለምህረት እንታገላለን፡፡

በብዙ መልኩ ተስፋ የተጣለበት የሀገራዊ ምክከር መድረኩ፡- ፅንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ትጥቅ የሚፈታበት፤ ከትርክት ጦርነት ወጥተን የወንድማማችነትን እሴት ያዳበረ ትውልድ ግንባታ መሰረቱ የሚጣልበት፤ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት ግንባታ እውን እንዲሆን የጋራ ሁለንተናዊ ስምምነት የሚደረስበት፤ … እንደመሆኑ መጠን መላ ኢትዮጵያዊያን በጉጉት ለሚጠብቁት ለታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር መድረክ የበኩላችንን አውንታዊ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

በሴራ ልክፍት እየናወዙ የለውጡ አካል ሆኖ መቀጠል አይቻልም!

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
የካቲት 03/2014
ባሕር ዳር-ኢትዮጵያ

Exit mobile version