Site icon ETHIO12.COM

የመጨረሻው መጀመሪያ !!

ይህ ትውልድ “ወይም “እኛ ” በእርግጥም ለበጎና አገርን ለመገንባት ለሚጠቅም ተግባር በሙሉ ፤ በእርግጥም ከግዜ እና ታሪክ ጋር ግብግብ ለመግጠም ጊዜ የማናባክን ይልቁንም ከግዜ ጋር የታረቅን የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች ነን !!!

አስቀድሜ ይህንን የኢትዮጵያውያንና የመላዉ አፍሪቃውያንን አልሞ የማድረግ ብቃት በታላቅ ከፍታ ያስቀመጠ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ መገባደጃው የመድረሱን መጀመሪያ በሚያበስረው የመጀመሪያው ምእራፍ የሐይል ማመንጨት መርሐ ግብር ስነስርዓት ላይ ተገኝቼ ፤ ይህንን በታሪክ የሚሰጥ ልዮ እድል የኢኤሓ የስራ አመራር ቦርድን ወክዬ ንግግር እንዳደርግ እድል ለሰጠኝ ለፈጣሪ ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንዲሁም ለክቡር ጠ/ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ ምስጋናዬን ሳቀርብ ደስታዬ ወደር የለውም።

” እኛ አሁን ለመገንባት አቅሙ ላይኖረን ይችል ይሆናል ነገር ግን ዛሬ እኛ በምናስቀምጠው ራእይና አቅጣጫ ፤ ነገ ከነገ ወዲያ ልጆቻችን ይገነቡታል “

ቀዳማዊ ፤ ዓፄ ፤ ኃይለ ስላሴ 1957 ዓ.ም የተናገሩት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ከጥንስሱ አሁን እስከ ደረሰበት የአፈፃፀም ምእራፍ በርካቶች በየደረጃው ለአገራቸው እድገት ፣ ልእልና እና ፍትህ ለሰፈነበት የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ያላቸውን ጥልቅ ቁጭትና ቁርጠኝነት በየዘመናቸው ያንፀባረቁበት ይህንንም ቁጭት በተግባር ወደሚታይ ውጤት ለመለወጥ መስዋእትነት የከፈሉበትና በአመራር ትውልዶች ቅብብል እየተገባደደ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ቀደም ሲል ከጠቀስኩት የንጉሱ ንግግር እንዲሁም ፕሮጀክቱን በይፋ በ2003 ዓ/ም ባስጀመሩበት ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ካደረጉት ታሪካዊ ንግግርና፤

ሌሎችም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በተለያዮ ጊዜያት የቀረቡ ልዮ ልዮ መልእክቶችን በመመርመር መረዳት እንደሚቻለው፤

በእርግጥም “ይህ ትውልድ “ወይም “እኛ”​ለበጎና አገርን ለመገንባት ለሚጠቅም ተግባር በሙሉ ፤
በእርግጥም ከግዜ እና ታሪክ ጋር ግብግብ ለመግጠም ጊዜ የማናባክን ፤ ይልቁንም
ከግዜያችንም ይሁን ከአባትና እናቶቻችን ዘመን ጋር የታረቅን ፤ የእናቶቻችንና የአባቶቻችን ልጆች የመሆናችን እውነታ ጥርት ብሎ ይታያል!!!

የህዳሴው ፕሮጀክት ግንባታ በሐይል ማመንጨት የኢንጂነሪንግ ሙያ ዘርፍ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፋት ጥቂት አመታት እያካበተች የመጣችውን ልምምድና ፣ የላቀ የሙያ ሽግግር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ ያስቻለ ፤ የአገር ውስጥ የሙያ አቅምን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኘ ወሳኝና ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ ከሐይል ማመንጨት ኢንጂነሪንግ ከፍተኛ የእውቀት ሽግግር ስራዎች ጋር በተጓዳኝ በምህንድስና እና የግንባታ ዘርፍም ውስብስብ የሲቪል ምህንድስና እንዲሁም የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮሜካኒካል ስራዎች የተከናወኑበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል።

ባለፋት አመታት ፕሮጀክቱ በየደረጃው በርካታ ውስብስብና አሳሳቢ የፕሮጀክት የአፈፃፀም ችግሮች ፣ የኮንትራት አስተዳደርና የፕሮጀክት አመራር ጉድለቶች ያጋጠሙትና
እነዚህንም ውስብስብ ችግሮች ፤ በትእግስትና በብስለት በተለያዩ ግዚያት የማስተካከያ እርምጃዎች በመውሰድ ለዛሬው የመጀመሪያ ምእራፍ ሐይል ማመንጨት ስራ መብቃቱን መመልከት ለታደልን ሁሉ እጅግ የሚያስደስት ሲሆን ፤

ለፕሮጀክቱ መሳካት በቅንነትና በሐላፊነት ብዙ ለጣሩ ፣ ለደከሙና ይህንን መጨረሻ አስቀድመው በምናባቸው ላዩ የዚህ ፕሮጀክት ጥንስስና አመራር ሰፊ ተዋናዮችም በሙሉ
ይህ የመጀመሪያ ምእራፍ ሐይል የማመንጨት ስራ ማስጀመሪያ (የመጨረሻው መጀመሪያ) ስነ ስርአት በእርግጥም ቃላቸው ተግባራቸው እና መስዋእትነታቸው በዚህ ትውልድም ተከብሮና ተጠብቆ ክፍተቶቻቸው ደግሞ በሚገባ ታርመው ፤ ፕሮጀክቱ ከፖለቲካ መጠቀምያነት አስወጥቶ ወደ እውነተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራ የቀየረና የዛሬው ፍሬ እንድናይ ያደረገ ለህዝብ እና ለእውነት የቆመ መንግስት መኖሩን ያረጋገጠ፤

ፕሮጀክቱን ፍሪያማ ለማድረግ የቆረጡ በአገራችን የሀይል አቅርቦትና ልማት የምህንድስና ዘርፍ ለአገራቸውና ለራሳቸው ጉልህ አበርክቶ ባደረጉ በእነ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ እና መሰል ጛደኞቻቸው እግር የተተኩ፤ አዲስ የፕሮጀክትና የአገር አመራር ትውልድ መፈጠሩን የሚያበስር ኩነት መሆኑን በሙሉ ልብ ማረጋገጥ እችላለሁ።

እዚህ ላይ በተለይም ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ውስጥ በፕሮጀክቱ አመራርና የመሬት ላይ አፈፃፀም በተመለከተ ቀደም ብለው ተከስተው የነበሩ ጉልህ እና ውስብስብ የፕሮጀክት አያያዝና የአመራር ክፍተቶች የታረሙበትና መልሶም ፕሮጀክቱን ከስም አልፎ ዛሬ ለበቃበት ደረጃ ለማድረስ የተሰሩ ውስብስብ ስራዎችን መላው ያገራችን ህዝብ እንዲገነዘበው ማድረግ ያስፈልጋል።

በፕሮጀክቶች አያያዝና ጉልህ የቀደሙ እክሎች ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ያለምንም ድንጋጤ ችግሮችን ከመሸፋፈን ይልቅ ፣ ችግሮችን ተቀብሎ በጊዜያዊነት በማስተዳደር በመጋፈጥና በአፋጣኝም የፕሮጀክቱን አያያዝና አፈፃፀም የሚቀይሩ ፣ የተጠኑና በንድፈ ሀሳብ ጭምር የተደገፉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስገደዱ ቅርቃሮችም በየስራው ዘርፍ በስፋት አጋጥመው እንደነበር ለማስታወስ እወዳለሁ።

ፈረንጆቹ ፤ When you are going through the hell , don’t stop / Keep Going / !! ይላሉ፤
ወደ አማርኛ ሲመለስ ከሞላ ጎደል
“በሲኦል ጉሮሮ ውስጥ በምትሔድበት ግዜ ሁሉ የሚሻልህ ያለመቆም ነው “

በእነዚህ የቀውስ ጊዜያት የተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎችም በፕሮጀክት አመራር ስራዎች ጥናትና መስክ የፕሮጀክት ስራ ተግዳሮቶች ቅልበሳ “project turnaround ” ልዩ ልምምድ የተቀመረበት በመሆኑ ፤ በየትኛውም ደረጃ ለሚያጋጥሙ የፕሮጀክት አያያዝና አፈፃፀም ችግሮች ተጠቃሽ ማሳያነቱን እንደ አስፈላጊነቱ ፣ በሚመለከታቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ተመራማሪ አካላት ጥናት ቢደረግበት ጠቃሚ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

የህዝባችንና የሃገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በቀጣይነት ለማሟላት እና በየአመቱ በአማካይ በ13% እያደገ የመጣው የሃገራችን የሀይል ፍላጎት መመለስ እንድንችል አሁን ካሉን እና እየገነባን ካለናቸው የሃይል ማመንጫዎች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ተጨማሪ የሃይል ምንጮች እና ፕሮጀክቶች ቀርፆ መተግበር እንደሚያስፈልግ መረዳትም ያስፈልጋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአመት 15,760 ጅጋ ዋት ሰዓት ሓይል በማመንጨት የሀገር ውስጥና የኤክስፖርት ፍላጎቶች ለማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።

ዛሬ የሐይል ማመንጨት ስራውን የሚጀምረው የፕሮጀክቱ ክፍል በመጀመርያው ተርባይን በመጠቀም ሐይል የማመንጨት እቅዳችን የሚያሳካ አፈፃፀም ሲሆን ፕሮጀክቱ ከሐይል ማመንጭት በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃና የቱሪዝም ልማት ዙርያ በቀጣይነት በፕሮጀክቱ የሚካተቱ ግዙፍ ተያያዥ ስራዎችም በአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ሌላ ጠንካራ የኢኮኖሚ ስበት ማእከል መፍጠር የሚያስችሉ ፣ የጎለበቱ ውጥኖችን ያካተተ መሆኑን በአንክሮ ማስተዋል ይገባል።

ፕሮጀክቱን በሚመለከት ከተለያዮ አቅጣጫዎች ከውስጥም ከውጭም ከቅርብም ከሩቅም፤ ከፕሮጀክቱ ዓላማና እውነታ በተፃራሪ ደም በለበሱ የምቀኝነት አይኖች የመታየቱ ምክንያት ምን እንደሆነም በአስተውሎታችን ልክ ሊገለፅልን ይችላል ።

ይህ ፕሮጀክት በቀጣይ ተከታታይ ወራት በየምእራፉ እንዲጠናቀቅ የሚያግዙ በርካታ ስራዎች ከስር ከስር እየተከናወኑ ያሉ በመሆኑ በተከለሰው የፕሮጀክቱ የማጠናቀቂያ የግዜ ሰሌዳ መሰረት ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ወደተሟላ የሀይል የማመንጨት ስራ የሚሸጋገርም ይሆናል።

ይህ ፕሮጀክት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ልቡን የጣለበት የጋራ ቁጭቱ መቋጫ ጫፍ የሚደርስበት መሆኑን ለአፍታ ሳይዘነጉ ፤ በእጅግ አስቸጋሪ የአየር ጠባይና ከፍተኛ ሙቀት ሳይበገሩ ፤ ሌት ተቀን ጉልበትና እውቀታቸውን ያለስስት ላለፉት በርካታ አመታት ላበረከቱና እያበረከቱ ለሚገኙ የጉልበት ሰራተኞች ፣ በልዩልዩ የግንባታና የቴክኒክ እንዲሁም በአጋዥ አገልግሎት ስራዎች የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ መሐንዲሶች እና ልዮልዮ ሙያተኞችን ከልብ እናመሰግናለን ።

ለመላው የአገራችን ህዝቦች፣ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጆች ይህ ፕሮጀክት እዚህ እንዲደርስ በሀሳብ ፣ በገንዘብ ፣ በእውቀት ያላችሁን ሁሉ ሳትሰስቱ በማበርከታቹ ሁሌም በማይፋቅ የታሪክ መዝገብ ውስጥ ተመዝግባቹሃልና እንካን ደስ አለን።

የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሀይሎችና ፣ የኢፌዲሪ የመከላከያ ሀይላችንን ደግሞ በተለየ ከልብ እናመሰግናለን ።

ልዮልዮ የክልልና የፌደራል መስሪያቤት ሀላፊዎች እና አመራሮች ፤ በአጠቃላይ ይህንን ፕሮጀክት እዚህ አመርቂ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ልዩ እገዛ ላደረጉ ሁሉ የላቀ አክብሮትና ምስጋናዬን ሳቀርብ ፤ የፕሮጀከቱ ቀሪ ስራዎች ተገባድደው ወደ መጨረሻ ምእራፍ እንዲደርስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አሁንም እንደ ወትሮው ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትላቸው እንዳይለየን አደራም በማለት ጭምር ነው።

በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድባችን አፈፃፀም ሂደት የመጨረሻው የመጀመሪያ የሆነውን ይህን የስኬት ምእራፍ እና ቀጣይ ውጤቶቻችንን በተቀሩት ቁልፍ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ለመድገምና ለመደጋገም የሚያስችለን ጥበብ፣ ስክነትና ፣ አንድነትን፣ ፈጣሪ እንዲሰጠንና በጥቂት አመታት ውስጥእንደ ህዝብ ወደ ምንመኘው ክብር እንደምንሸጋገር በሚያረጋግጥ መንገድ ላይ ስለመሆናችን በሚያሳይ ፅኑ እምነትና ፍላጎት ላይ ሆኜ ፤ ሁላችንንም በድጋሚ፤ እንኳን ደስ አለን ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ህዝባችንን ይጠብቅ ፤ ይባርክ !

አመሰግናለሁ!! Dr Abraham Belay

Exit mobile version