Site icon ETHIO12.COM

በኢትዮጵያና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር ጸጥታን በጋራ ለማስከበር ባለስልጣናቱ መከሩ፣ ከኬንያ ጋር ስምምነት ተደርሷል

በጁባላንድ ክልል የሰላም ሁኔታ እና በኢትዮጵያና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች በፀጥታ ጉዳይ አብሮ ለመሥራት ውይይት ተካሄደ። የጁባላንድ ክልል ፕሬዝዳንት፣ የሴክተር 3 አዛዥ፣ የሴክተር 6 አዛዥ፣ የ5ኛ ሞተራይዝድ ዋና አዛዥና የጁባላንድ ክልል ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የመረጃ ኃላፊ በውይይቱ ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

ውይይቱን የመሩት የጁባላንድ ክልል ፕሬዝዳንት አህመድ መዶቤ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ የሚመሳሰሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህንን አንድነታችንን እና ወንድማማችነታችንን በመሸርሸር ዓላማውን ለማሳካት አልሸባብ ሌት ከቀን እየጣረ ይገኛል ብለዋል። በመሆኑም እስከ ዶሎ ያሉትን ቦታዎች በመቆጣጠር በጋራ በመሆን መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የሴክተር 3 አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ፣ በሶማሊያ የጠላት ሽብርተኝነት፣ የጎሳ ግጭት እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አለመግባባት ይስተዋላል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ በጌድዮ ዞን በሕዝቡ ዘንድ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩትን አካላት በጋራ ሆኖ በመለየት የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን ብለዋል።

የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ ከሕዝቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራት እንደሚገባ፤ የአልሸባብን ተንኮልና ሴራ ቀድሞ በመረዳት አከርካሪውን መስበር እንደሚያስፈልግ የሴክተር 6 አዛዥ ብ/ጄ አበባው ሰይድ እና የ5ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰፋ መኮነን መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ኬንያ በከፍተኛ የፖሊስ ኮሚሽነሮቻቸው አማካይነት አዲስ አበባ ላይ መክረው በጋራ ድንበራቸው አካባቢ አሉ የሚባሉትን ጸረ ሰላም ሃይሎች በስም ጠቅሰው ለማደን ከስምምነት መድረሳቸውን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ከወር ባነሰ ጊዜ የፊርማ ስምምነት አድርገው ወደ ስራ እንደሚገቡ ማስታውቃቸው ይታወሳል።

Exit mobile version