Site icon ETHIO12.COM

“… ርሃብ ግን የስንፍናችን ውጤት ነው” – ዐቢይ አህመድ

በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖች ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት
ጥሪ አቅርበዋል።

“ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን የሥንፍናችን ውጤት ነው” በሚል ርዕስ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ “በመኖና የውሃ እጦት ከብቶቻቸው እየረገፉ ነው። ድርቁ ያስከተለው ርሃብ የሕጻናቱንና የአረጋውያኑን ሕይወት እያሳጣ ነው። ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን” ብለዋል።

ለድርቅና ርሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተረባረብን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖቻችንም አቅማችን የፈቀደውን እንድናደርግ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

“ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን የሥንፍናችን ውጤት ነው” በየአሥር ዓመቱ እየተመላለሰ እንደሚጎበኘን ድርቅና ርሃብ ልክ በታሪካችን የፈተነን ጠላት የለም። አያሌ ውድ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል።

በምግብ ራሳችንን ያለመቻልችግር ህጻናትን ለመቀንጨር፣ ወጣቶችን ለስደት፣ አረጋውያንን ለጉስቁልና፣ የቀንድና ጋማ ከብቶቻችንን ለእልቂት ዳርጓል።

ቅኝ ሊገዙን የመጡ የውጭ ወራሪዎች በርሃብና ቸነፈር ልከ እልፈተኑንም። ዳር ድንበራችን እንዳይነካ፣ ሉአላዊነታችን እንዳይደፈር የምናድርጋቸው ተጋድሎዎች በርሃብና ቸነፈር ላይ አለመደገማቸው ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን አስረጅ ኢያሻውም።

ርሃብ የሀገራችን ምስል ላይ ጥቁር ነጥብ ኣስቀምጦአል። በምግብ ራሳችንን ባለመቻላችን ምከንያት ብሄራዊ ህልውናችን ጥላ እጥልቶበት መታየቱ ሊቆጨን ይገባል።

የእለት ጉርሳችንን አሸንፈን እስካልተገኘን ድረስ በየትኛውም ዘርፍ የምናስመዘግበው ስኬት ትርጉሙ ይደበዝዛል።

ግብርና ምርቶች ላይ የምናሳየው ድከመት በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊም፣ በፖለቲካውም፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተጽእኖ አለው።

ለግብርና ተስማሚ ለም መሬትና ወንዞች ኖረውን የእርዳታ በሮችን የምናንኳኳው፣ ታሪከ ኖሮን ጎልተን የማንታየው፣ እምቅ የዲፕሎማሲ አቅም እያለን በዓለም መድረኮች የማንደመጠው- በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ – ጊዜ እየጠበቀ በሚጎበኘን ድርቅ እና ርሃብ ምከንያት ነው።

ተደጋግሞ እንደሚባለው ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን ሰው ሠራሽ ነው፣ ሥንፍናችንና ደካማ የግብርና ፖሊሲዎቻችን የፈጠሩት ችግር ነው።

በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ፣ በዘላቂነት ከርሃብና ቸነፈር የመላቀቅ ጉዞ ለጥቂቶች የሚተው፣ ወይም ለጥቂት ጊዜ የሚቀነቀን አጀንዳ አይደለም፤ እንደ ሀገር ተባብረን ልናሸንፈው የሚገባ የጋራ ጉዳያችን ነው።

ገልጠን፣ መርምረንና ለፍተንበት የምንለውጠው እንጂ ሸፋፍነንና ደብቀን ፈጽሞ ሊንሻገረው አንችልም።

ያለን ምርጫ እንድ ነው፤ ተረባርበን ዘላቂ መፍትሄ መስጠት። ባንኮች ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አርሶ አደሩና አርብቶ እደሩ የቆጠበውን ገንዘብ ተጠቅማችሁ የአገልግሎትና የግንባታው ዘርፍን ፋይናንስ በማድረግ በዚያ በኩል ለውጥ እንዳመጣችሁ ሁሉ፥ ግብርናውንም ፋይናንስ በማድረግ የምትከሱበትን መንገድ መቀየስ እለባችሁ።

ከምርጥ ዘርና የግብርና ግብዓትና መሳሪያዎች አቅርቦት ጋር በተገናኘ መሥራት ለሚደልጉ አካላት ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን መንግሥት ያዘጋጃል።

በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮችም ሆኑ፣ በሠፋፊ የመስኖ ግብርና ላይ የሚሠማሩ የግል ኢንቨስተሮች በተለያዩ መንገዶች ይበረታታሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ በአሁኑ ሰዓት በድርቅ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ የሶማሌና የቦረና አርብቶ አደር ወገኖቻችን እፋጣኝ እርዳታችንን ይሻሉ።

በመኖና የውሃ እጦት ከብቶቻቸው እየረገፉ ነው። ድርቁ ያስከተለው ርሃብ የሕጻናቱንና የአረጋውያኑን ሕይወት እያሳጣ ነው። ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን።

ለድርቅና ርሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተረባረብን፣ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖቻችንም አቅማችን የፈቀደውን እንድናደርግ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!! ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

Exit mobile version