Site icon ETHIO12.COM

ኤታማዦር ሹም ትህነግ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን የሚፈታ እርምጃ ለመውሰድ እየተገደዱ መሆኑን ይፋ አደረጉ

አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ የተሰጠውን እድል ተጠቅሞ የሰላም አማራጭን የማይዝ ከሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን የሚፈታ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ የኢፌዴሪ ጦርኃይሎች ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

ከራያ ተራራዎች እስከ ቆላ ተምቤን ከሰሜን እዝ እስከ አፋር ግንባር በመሳተፍ የላቀ ጀግንነት እና ጀብዱ ለፈፀሙ የምስራቅ እዝ አባላትና አመራሮች ሽልማትና የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል።

ትላንት በሰመራ ከተማ በተካሄደው የምስራቅ እዝ የእውቅናና የሽልማት መርሐግብር ላይ የጦርኃይሎች ኢታማዦር ሹሙ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ ስህተት ሲፈጽም የነበረ እና ዛሬም ሌላ ስህተት እየፈፀመ ያለ ከስህተቱ የማይማር ቡድን ነው።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ የሰሜን ዕዝን ከማጥቃት አንስቶ በርካታ ስህተቶችን መፈፀሙን ጠቁመው፤ ከዚያ በኋላ በጠንካራ የኢትዮጵያ ጀግኖች ክንድ አከርካሪው ቢሰበርም ዛሬም በአፋር በኩል ትንኮሳ በመፈፀም የውጭ አጋሮቹን ድምፅ ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት ይህ ቡድን የኢኮኖሚ አቅሙ ተሟጧል፤ የትጥቅ አቅሙ ተዳክሟል፤ የሰው ኃይል ኪሳራም ደርሶበታል፤ ሆኖም አሁንም ለሌላ ጥፋት የሰው ኃይል እያሰባሰበ ይገኛል። ይህ ደግሞ ዳግም የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ካልሆነ ሌላ ፋይዳ የለውም ብለዋል።

በመሆኑም እኛ በተደጋጋሚ የሰላም እድል ሰጥተናል፤ የትግራይን ልጆች ዳግም እንዳያስጨርስም አሳስበናል፤ ሆኖም ቡድኑ ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይገባ በማድረግ የዓለምን ትኩረት በመሳብ በሰው ልጆች ስቃይ ትኩረት ለማግኘት እየጣረ ነው ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እንደገለጹት፤ አገራችን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል እንደአገር ለመቀጠል የታገለችበት እና ጠላቶችም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተናነቁበት ወቅት ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዳይሞላ ብዙ ትግል ተደርጓል፤ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለመውሰድ ተሞክሯል፤ የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ለመቀማት የሚፈልጉ ኃይሎች ብርቱ ትንቅንቅ አድርገዋል ብለዋል።

እኛም ስንታገልና መስዋዕትነት ስንከፍል የቆየነው ይህ እውን እንዳይሆን እና አገራችን ሰላሟ ተጠብቆ እንዲቆይ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የምስራቅ እዝም ከሌሎች እዞች ፤ ከአፋርና ከአማራ ሚሊሻና ልዩ ኃይል፤ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ጠቁመዋል። 

የምስራቅ እዝ ቀደም ሲል በምስራቅ በኩል ለብዙ ዓመታት ከአልሸባብ ጋር ሲታገል የቆየ የሰራዊቱ ክፍል ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነትም ከምስራቅ ተወርውሮ ከራያ እስከ መቀሌ የገሰገሰ፤ በሽሬ በኩልም ተምቤን ዋሻ ድረስ ዘልቆ በመግባት የአሸባሪው ህወሓትን ሽፍቶች አድኖ የያዘ ጦር እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላም ድሬ ዋቃ ላይ ለወራት የዘለቀ የመከላከል ሥራ የሰራ፤ በካሳጊታ ግንባርም ጠላት ወደሚሌ ለመግባት በተደጋጋሚ ያደረገውን ሙከራ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ያከሸፈ፤ በካሳጊታ ግንባር ጠላት በተከታታይ ለ22 ቀናት ጥቃት ሲፈጽም ቀንና ሌሊት ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ ድል ያስመዘገበ እንደሆነም ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ አገራቸውን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች በመከላከልና በመጠበቅ የረጅም ጊዜ የጀግንነት ታሪክ ያለው የአፋር ሕዝብ እና ከዚሁ አብራክ የወጡት የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ለተገኘው ድል ትልቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “ሽልማቱም ሆነ የማዕረግ እድገቱ የተሰጠው ለጥቂት አባላት ቢሆንም እነሱ የሚወክሉት ክፍል ሁሉ የሽልማቱ አካል በመሆኑ ሁላችሁም እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ለቀጣይ ተልዕኮና ድል ተዘጋጁ” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በትናንትናው መርሐግብር የተሰጠው ሽልማት በምርጥ አዋጊ፤ በምርጥ አዋጊ በግለሰብ፤ በምርጥ ተዋጊ በዩኒት፣ በድጋፍ ዘርፍ እና በስታፍ ዩኒት ሲሆን በአጠቃላይ 154 ግለሰቦችና ቡድኖችን ያካተተ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ወርቁ ማሩ

አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014

Exit mobile version