Site icon ETHIO12.COM

ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ለአመራርና ሠራተኞች ሲሰጥ የነበረን የገንዘብ ብድር በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በየደረጃው ያለው አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር ለዋናው ዓላማችን ስኬት ማለትም ለክልላችንና በአጠቃለይም ለሀገራችን ብልጽግና ተግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ከሠራንባቸውና ጉልህ ስኬት ካስመዘገብንባቸው ጉዳዮች አንዱ ብቁ አመራርና የፓርቲ መዋቅር ለመገንባት የሠራነው ተግባር ነው፡፡

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በቀጣይነትም የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲውን በማጠናከር የፓርቲያችን አስተሳሰብ፣ አደረጃጃቱንና በአጠቃላይም አባላቱን ለማብቃት እየሠራ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ፓርቲያችን የአመራሩንና የአባላቱን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብና አቅም በተከታታይነት ለማብቃት ጥረት ከማድረጉም በላይ መታረም የሚገባቸውን የተቋም፣ የአመራርና የአባላት ጉድለቶች ጊዜ ሳይሰጣቸው እንዲታረሙ የማድረግ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህን የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የማጠናከር ሥራ የምንሠራው ፓርቲያችን የተፈጠረው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በመሆኑና የትኛውም ዓይነት መታረም ያለበት ተግባር በወቅቱ ካልታረመ የብልጽግና ጉዟችንን ያደናቅፋል የሚል ዕምነት ስላለን ነው፡፡

ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ማጠናከር ሥራችን አንዱ የፓርቲውን አሠራርና መመሪያ ማጠናከርና ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፓርቲው ሃብት የሆነ ተቀማጭ ገንዘብ ለአመራሮችና ሠራተኞች የረጅም ጊዜ ብድር አሠራር ስርዓት በመዘርጋት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመዋዋል ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይኸው አሠራር ከፓርቲ የገንዘብና ሃብት አስተዳደር ስርዓት አኳያ ህገ ደንቡን የሚጣረስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የውሳኔ አሰጣጥና የስራው አፈፃፀም ከፓርቲው ህገ ደንብና አሠራር ጋር የሚቃረን መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

በመሆኑም በብድር ስም የወጣው የፓርቲው ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነ ወለዱ ታስቦ ተመላሽ እንዲደረግና ዝርዝር ሁኔታው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራርና ሰራተኞችም ከያዙት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት ከየካቲት 25/2014 ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ለአሰራሩ ተገዥ በመሆን ተፈፃሚ የማያደርጉ ግለሰቦች ካጋጠሙ በህጉ መሰረት ተጠያቂነታቸው የሚከናወን ይሆናል፡፡

ይህ የማጣራትና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በፓርቲው ህገ ደንብና አሰራር መሰረት በኦዲት ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን መርማሪነት የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢነት ተመስርቶ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ መርምሮ ውሳኔ የሰጠበት ሲሆን ዝርዝር ሁኔታው በፓርቲው የውስጥ አሠራር መሰረት ለመላ የፓርቲው አባላትና አመራሮች በተዋረድ በግልጽ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
የካቲት 25/2014 ዓ.ም
ባሕር ዳር

Exit mobile version