Site icon ETHIO12.COM

የሶማሊያ የጸጥታ ኃይል የአገሪቷን ሰላም የማስከበር ኃላፊነት ከአሚሶም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊረከብ ነው

የሶማሊያ የጸጥታ ኃይል የአገሪቷን ሰላም የማስከበር ኃላፊነት በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ (አሚሶም) ሊረከብ መሆኑ ተገለጸ።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ባዘጋጀው የጊዜና የግዳጅ አፈጻጸም ማዕቀፍ አማካኝነት የሶማሊያ የጸጥታ ኃይል የአገሪቷን ጸጥታ የማስጠበቅን ሙሉ ኃላፊነት በሁለት ዓመት ውስጥ ከአሚሶም እንደሚረከብ ዘ ኢስት አፍሪካን ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።

የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ (አሚሶም) ስያሜ ወደ ሶማሊያ የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ እንደሚቀየርም ተገልጿል።

ተልዕኮው የሶማሊያ ምድርና አየር ኃይሎች እንዲሁም የስለላና ደኅንነት ተቋማትን አቅም መልሶ በመገንባት በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ኃላፊነታቸውን እንዲወስዱ የማዘጋጀት ሥራ ያከናውናል ተብሏል።

በሽግግሩ ዙሪያ የአፍሪካ ኅብረትና የሶማሊያ መንግሥት ከመግባባት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በያዝነው ወር ላይ ማዕቀፉን ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘ ኢስት አፍሪካን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል።

ከ15 ዓመት በላይ የቆየው አሚሶም ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲና ጅቡቲ የተወጣጡ 20 ሺኅ የሚጠጉ ወታደሮችን የያዘ ኃይል ነው።

እንደ አሚሶም መረጃ ከሆነ ኡጋንዳ 6 ሺህ 223 መለዮ ለባሽ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በሶማሊያ በማሰማራት ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።

ብሩንዲ 5 ሺሕ 432 እንዲሁም ኢትዮጵያ 4 ሺሕ 395 ሰላም አስከባሪዎችን ለተልዕኮው ማበርከታቸውን ገልጿል።

walta

Exit mobile version