Site icon ETHIO12.COM

“ብልህ የፖለቲካ መንገድ…የሰከነ የፖለቲካ ባህልን መምረጥ ያዋጣል” ይልቃል ከፋለ

“ፖለቲከኞቹ አሁን የምንሄድበት መንገድ የነገን የአማራ ሕዝብ መሻት ይወስናልና

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውይይቱን እያካሄደ ነው፡፡ የምክር ቤት አባላቱ በውሎሏቸው ትናንት የቀረበውን የርእሰ መስተዳድሩን የስድስት ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት አድርገው ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ የአማራ ሕዝብን የማፈናቀል ድርጊት አስመልክቶ ከምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ የተነሳላቸው ርእሰ መስተዳድሩ የችግሩ መነሻ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የተሠራ የተሳሳተ ትርክት ውጤት ነበር ብለዋል፡፡

ችግሩ አሁን የመጣ እና ወቅታዊ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ችግሩ ሲፈጠር ብዙዎቻችን በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊዎችም ነበርን ብለዋል፡፡ የተሻለው አማራጭ ችግሩን ለማስቆም የሰላም አማራጮችን ማየት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአማራ ወንድም ሕዝቡ ጋር ችግር እንደሌለበት በሰሞኑ የብልጽግና ሕዝባዊ ውይይት ወቅት አይተናል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል የፖለቲካ ልሂቃኑ ችግሮችን ከማባባስ ወጥተን የመፍትሔ አማራጮችን ማየት ይገባል ነው ብለዋል፡፡

ከሕገ መንግሥት መሻሻል ጋር ተያይዞ ርእሰ መስተዳድሩ ሲመልሱ ብልጽግናም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ አይሻሻልም የሚል አቋም እንደሌላቸው ገልጸው ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ባሳተፈ መልኩ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም የአማራ ሕዝብ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ቁስል እንዲታይ ከወዲሁ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በሕገ መንግሥቱ የተሳሳተ ትርክት ዋጋ ሲከፍል ቆይቷል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ይህንን ችግር በሕገ መንግሥት ለመመለስ መልካም ግንኙነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“ፖለቲከኞቹ አሁን የምንሄድበት መንገድ የነገን የአማራ ሕዝብ መሻት ይወስናልና የሰከነ የፖለቲካ ባህልን መምረጥ ያዋጣል” ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ በምላሻቸው፡፡
የአማራን ሕዝብ የዘመናት ቁስል እኛ ከምንናገር ሌሎች እንዲያዩት ማድረግ ብልህ የፖለቲካ መንገድ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የሌሎችን ቁስል ማየት ደግሞ የአማራ ሕዝብ ነባር የታላቅነት እሴት ነው ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም ብቸኛው መንገድ በጋራ መቆም ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በጋራ እድንቆም እና የአማራ ሕዝብን ማሕበራዊ ፈተናዎች ለመሻገር በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:–ታዘብ አራጋው – (አሚኮ)

Exit mobile version