Site icon ETHIO12.COM

ይድረስ ለአማራ አክቲቪስቶች – ወልቃይት ጠገዴና ሁመራ የሰላም አስከባሪ እንዲገባ ተጠየቀ

የጎንደር ዩኒቨርስቲ “ሕወሓት ባለፉት 40 ዓመታት ከ60 ሺህ በላይ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎችን በማንነታቸው እየለየ ጨፍጭፏል” ሲል የጥናት ግኝቱን ይፋ ባደረገ በቀን ልዩነት አምነስቲና ሂይውማን ራይትስ ዎች ወልቃት ጠገዴ ( ትህነግ ከአማራ ክልል ነጥቆ ምዕራብ ትግራይ) ያለውን አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲሰፍርበት ሲል በሪፖርቱ ጠየቀ። ዜናው አማራ ክልልን እያተራመሱ ላሉ “አክቲቪስት ነን” ለሚሉ ወገኖች ” እንኳን ደስ አላችሁ” አሰኝቷል።

የአማራ ክልል ጉልበቱን ሁሉ አንድ ጉዳይ ላይ አሳርፎ በትኩረት እንዳይሰራ ዓላማውና የመጨረሻ ፍላጎቱ ግልጽ ያልሆነ ቅስቀሳ እያካሄዱ ያሉ አክቲቪስት ነን ባዮች እንቅፋት እንደሆኑበት ሲያስታውቅ መክረሙ ይታወሳል። ሕዝቡን በመከፋፈልና እንዲምታታበት በማድረግ ላይ ትኩረት አድርገው የክልሉን መንግስት ጉልበት እያዝሉ ያሉት ወገኖች ዛሬ ይፋ በሆነው “የዘፈን ዳርዳሩ” ዜና “ስለቴ ሰመረ” የሚል ዜማ እንዲያሰሙ የጠየቁም አሉ።

“በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች ከ12 በላይ የጅምላ መቃብሮ ተገኝተዋል” ሲል የጎንደር ዩኒቨርስቲ ይፋ ባደረገው ጥናት ላለፉት አርባ ዓመታት እስከ ስልሳ ሺህ አማራዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸው ይፋ ሲደረግ፣ በማይካድራ በቅርቡ ንጹሃን መታረዳቸው፣ በዳግም ወረራ አማራ ክልል አመድ ሆኖ፣ አማራ በማእዱ ላይ ታርቶበት፣ ማምለኪያው ረክሶ፣ ንብረቱ ተዘርፎ፣ እናት ልጆቿ ፊት፣ ልጆች ወላጆች ፊት ተደፍረው፣ በገሃድ ቤተሰብ ተረሽኖና መሰረተ ልማት ወድሞ… ይህ ሁሉ ደርሶ የአማራ አክቲቪስቶች የክልሉ ሕዝብ አንድ እንዲሆን ከማስተማርና ከመቀሰቀሰ፣ ዳግም እንዲህ ያለው ወረራ እንዳይከሰት የብረት ደጀን እንዲገነባ ከመወትወት፣ ጎን ለጎንም ሰላም እንዲወርድ ከመስራት ይልቅ ክልሉን አቅም አልባ ማድረግ ላይ፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እንዲናከስ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው ለበርካቶች እንቆቅልሽ መሆኑ በየጊዜው የሚገለጽ የቁጭት ድምጽ ከሆነ ሰንብቷል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ በጋራ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት “ምዕራብ ትግራይ” ሲሉ በሚጠሩት የቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ አማራ ርስት ላይ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰፍር ሃሳብ አቅርበዋል። በአማራው ላይ የተፈጸመውን ግፍ አጉልቶ ማሳየትና በእልህ ስሜት መታገል ሲገባ እርስ በርስ መተራመሱ በከፈተው ቀዳዳ የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲገባ ሃሳብ መቅረቡ እንደ ህዝብ አማራውን ለዳግም ጭፍጨፋና ቂም መወጣጫ አሳልፎ የሚሰጥ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘገበ ነው።

ድርጅቶቹ ከዓመት በላይ ፈጀ ባሉት ጥናት የትግራይ ተወላጆች ላይ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መከናውናቸውን ይፋ አድርገዋል። “ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች” ሲል ትህነግንና መንግስትን የጠራው ሪፖርት እነዚሁ አካላት የሚያደርጓቸው ስምምነቶች የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ወልቃይት ጠገዴ በፍጥነት ማሰማራትን የሚያካትት እንዲሁም ጥሪ አቅርበዋል። ሪፖርቱ በአፋርና በአማራ ክልል በዳግም ወረራ ስለተፈናቀሉ ስለተገደሉና የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው ወገኖች አላስረዳም። ጽድቅ ስለመሆኑም ትህነግን ጠቅሶ አላወገዘም።



በጥቅሉ የአማራና የትግራይ መስተዳድሮች በባለቤትነት በሚወዛገቡበት ምዕራብ ትግራይ ዉስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከል የዘር ማጽዳት  ተፈፅሟል። ድርጅቶቹ በመግለጫቸው እንዳሉት በአዲጉሹና ሑመራ 120 የትግራይ ተወላጆች በአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖና ልዩ ሐይል በጅምላ ተረሽነዋል። የሁለቱ ድርጅቶች ዘገባ በአወዛጋቢዉ  የምዕራብ ትግራይ ግዛት  የአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ሐይል እንዲሰፍር የጠየቀውም በዚሁ መነሻ ነው።

 የመቀለ ተወላጅ የሆኑትና ሚዛን የሳተ ሪፖርት በማቅርበ ብዙ ጊዜ የሚከሰሰኡትና ማስረጃም የቀረበባቸው የአምነስቲ የምሥራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተመራማሪ አቶ ፍስሐ ተክሌ ለጀርመን ድምጽ እንዳሉት ወንጀል መፈጸሙን ከ400 በላይ ሰዎች ማረጋገጣቸውን፣ በስፍራው ለመገኘትና ለማጣራት ፈቃድ መከለከሉን አመልክተዋል።

በሳምንቱ ከትናትናው ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ጥናቱን ያቀረበው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ይፋ እንዳደረገው ላለፉት አርባ አመታት ከአርባ እስከ ስልሳ ሺህ የአማራ ተወላጆች መጨፍጨፋቸውን አረጋግጧል።

ወልቃይት ጠገዴን ለማስከፈትና የሱዳን ኮሪዶርን ለመጠቀም በሃይል አልሳካ ሲል የተለያዩ ስልቶችን ሲጠቀም ለነበረው ትህነግ ይህ ዜና ታላቅ እንደሆነ ተመልክቷል። ዜናው “ተቆለፈብኝ” ለሚለው ትህነግ በገሃድ በር የማዘጋጀት ዓላማ እንዳለው ከወዲሁ የሚናገሩ የአማራ አክቲቪስት እነን የሚሉ ዳግም የውልቃይት ጠገዴን ሕዝብ አሳልፈው እንዳያሰጡት ስጋታቸውን ” እንኳን ደስ አላቹህ፣ ለሆዳችሁ አድራችሁ ሰርስሩን፣ አዋርዱን፣ አሳፍሩን” ሲሉ ገልጸዋል። እነዚህ ክፍሎች በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ችግር ካለ በሂደት መንቀስ እየተቻለ አንድነት በሚፈለግበት ወቅት በዚህ መልኩ ክልሉን ማተራመስ ዳግም የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወገኖች በህብረት መስራት አለባቸው የሚሉ ” ትህነግ ህዝብ ረሸነ፣ ዘር አጠፋ፣ በጅምላ አሰረ፣ አፈናቀለ፣ እየተባለ እየተከሰሰ ዳግም ንጹሃንን ለክ እሱ እንዳደረገውና ሲያደርግ እንደኖረው በትግሬነታቸው ብቻ ማጥቃት እጅግ ነውር ነው። መንግስት አጣርቶ ማንም ሳያዘው ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል። ማንም ይሁን ማን በዘሩ ጥቃት ሊደርስበት እንደማይገባ ከጥቂት ጎጠኛ ፖለቲከኞች በስተቀር ድፍን ኢትዮጵያዊያን ያምናሉ።

“ዛሬ ይድረስ ለአምራ አክቲቪስ ነን ባዮች” ሲል አስተያየቱን የላከው የክልሉ ተወላጅ ” የአማራ አክቲቪስት ነን ባዮች ዛሬ ነገሩን ቀልብሰው ወልቃይት ጠገዴ ለትግራይ እንዲሰጥ ብልጽግና ውስጥ ውስጡን ተስማማ የሚል መረጃ ሲረጩ እንደሚያድሩ ጥርጥር የለውም። ከሰሙ እረፉ በህዝብ ቁስልና ስሜት አትነገዱ በሉልኝ” ብሏል። የአማራ አክቲቪስቶች በገሃድ ግጭቱ የብልጽግናና የህወሃት ነው ሲሉ የመከላከያን መከዳትና መታረድ ሲያጣጥሉ እንደነበር ይታወሳል። የአማራ አክቲቪስት የሚባሉት በጽንፍ የቆሙት የሚታወቁትን ክፍሎች እንደሆነ አንባቢያን ይረዳሉ ተብሎ ይገመታል። ምርጥ የአማራ ተቆርቋሪዎች እንዳሉም ግልጽ ነው።

መንግስት ሪፖርቱን እንደሚመረምረው ጠቅሶ መግለጫ አውጥቷል።

በስብሃቱ አይንዓለም

Exit mobile version