Site icon ETHIO12.COM

“የመላዉ ሕዝብ የጸጥታ ስጋት…”

ሸኔና ፋኖን የመሠሉ ጽንፈኛ ሃይሎች የኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ክልሎችና የመላዉ ሕዝብ የጸጥታ ስጋት ስለሆኑ ሕዝቡ: አመራሩና የጸጥታ አካላት እነዚህን የጥፋት ሃይሎች በጋራ ሊታገል ይገባል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ተናገሩ።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ከአስተዳደር: ሕግና የሰዉ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ከክልሉ ጸጥታ አመራሮች ጋር በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን በተካሄዱ የህዝብ ዉይይቶችና ላይ ከፍተኛ ትኩረት አግኝተዉ ከተነሱና ምላሽ እንዲሰጥባቸዉ ከተጠየቁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መካከል የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ዋንኛዉ ነዉ።

ጨፌ ኦሮሚያም የክልሉ ሕዝብ የጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ሕዝቡ ባነሳቸዉ የሠላም ጥያቄዎች ዙሪያ ከክልሉ ጸጥታ አመራሮች ጋር ዉይይት አካሄዷል።

የክልሉ የጸጥታ አመራሮችም በክልሉ የሚታየዉን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሠሩ ባሉ ሕግ የማስከበር ስራዎች ዙሪያ የስራ ሪፖርት አቅርበዋል።

የክልሉ ጸጥታ ሃይሎች ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌደራል ፖሊስ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በሰሩት የኦፕሬሽን ስራ በቄለም ወለጋና በምዕራብ ወለጋ በአብዛኞቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች አበረታች ዉጤት መገኘቱን አንስተዋል።

ይህንኑ ኦፕሬሽን በምስራቅ ወለጋ: በሆሮ ጉዱሩ ወለጋና በሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች ለማስቀጠልም እየተሠራ ነዉ ብለዋል።

ጽንፈኛ ሃይሎች በክልሉ ሕዝቡ ላይ እየፈጸሙ ስላለዉ ጥፋት አስመልክቶ በቀረበዉ ሪፖርት ፋኖ የተባለዉን ቡድን ጨምሮ አንዳንድ ጽንፈኛ ኃይሎች የጦር መሳሪያ በመታጠቅና የክልሉን ድንበር ጥሰዉ በመግባት በንጹሃን ዜጎችና በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነዉ::

የሕዝቦችን ወንድማማችነት ስጋት ላይ እየጣሉ ነዉ ብለዋል። እነዚሁ ቡድኖች በአንዳንድ ከተሞች ላይ የሃይማኖትና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ እየተሯሯጡ መሆናቸዉንም አንስተዋል።

ከዉሃ: ከግጦሽ መሬትና ከተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አጎራባች ክልሎች ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባም አመራሮቹ አንስተዋል።

የቋሚ ኮሚቴዉ አባላትም በቀረበዉ ሪፖርት ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ለጠላት መረጃ በሚሰጡና የሥነ ምግባር ጉድለት በታየባቸዉ የጸጥታ አካላት ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ የጸጥታ አመራሮችም በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ለክልሉ ሕዝብ ሠላምና ደህንነት ሲሉ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ቢገኙም አንዳንዶች ግን የተጣለባቸዉን ሃላፊነት በመዘንጋት ሕዝቡን እያማረሩ ነዉ ብለዋል።

የሥነ ምግባር ጉድለት በታየባቸዉ የጸጥታ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰድን ነዉ ያሉት የጸጥታ አካላቱ ይህንን እርምጃም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የጸጥታ አካላቱንና ቋሚ ኮሚቴዉ ያወያዩት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱረህማን የክልሉን ጸጥታ ለማረጋገጥ በአንዳንድ ዞኖች የተጀመረዉ ስራ አበረታች ስለሆነ በሌሎች ዞኖችም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የሸኔ: የፋኖ ጽንፈኛ ኃይሎችና የሌሎች ጽንፈኛ ኃይሎች ዋና አላማ ኦሮሚያን ማፍረስ ነዉ ያሉት አፈ ጉባኤዋ የጸጥታ ሃይሎች: አመራሮችና የክልሉ ህዝብ የጥፋት ሃይሎቹን በጋራ ለታገል ይገባል ብለዋል።

የክልሉን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግ የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ጨፌ ኦሮሚያ ለክልሉ ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ ተገቢዉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ወንድማገኝ አሰፋ OBN

Exit mobile version