Site icon ETHIO12.COM

«ጀግናው ሠራዊታችን እንኳን ሊደፍሩት ሊጠጉት አስፈሪ ነው»

ጀግናው ሠራዊታችን የሕዝቡን ደኅንነት እና ልማት በደሙ ለማስከበር ወትሮ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል። ይሄንን ሕዝብና ሠራዊት በዓላማ አንድነት ያጸናውን ግንብ፣ እንኳን ሊደፍሩት ሊጠጉት አስፈሪ ነው።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ መጪውን የኢድ አልፈጥር በአል ምክንያት በማድረግ በወልድያ ከተማ ተገኝተው የመከላከያ ሠራዊቱን ጎበኙ።

“አብሮነታችን ለኢትዮጵያ አንድነት!” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የበአል አከባበር መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጪውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ የሚገኙትን የሠራዊት አባላትን ጎብኝተዋል።

በወልድያ ከተማ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየም በተዘጋጀው የበዓል አከባበር መርሃ ግብር ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የጦር ኃይሎች ም/ጠ/ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሠ፣ የሚኒስትር መስሪያ ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ የህዝብ አስተዳደር አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የበዓሉ አዘጋጅ የሆኑት የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ለዝግጅቱ ታዳሚዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት ለዘመናት የክርስትና እና የእስልምና ሐይማኖቶች በፍቅር የኖሩባት በመሆኗ አብሮነትን፣ መከባበርን፣ አንድነትን፣ ማካፈልን እና ከኢትዮጵያዊነት የመነጨ ፍቅርን ይገነባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይህም ጊዜና ዘመን የማይሽረው የእኛነታችን ብቻ መገለጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን የተረዱ የውጪ ጠላቶቻችንና የውስጥ ባንዳዎች ልማታችንን ለማደናቀፍ እና የአንድነታችንን ስር ለመበጣጠስ ቀን ከሌት እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ይህንን ማክሸፍ የሚቻለው የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው የሀገር ምሰሶ የሆነው መከላከያ ሠራዊቱን የማሸነፍ ሞራል ለመገንባትና ጉዳት ለመቀነስ ሁለንተናዊ ዝግጁነታችንን አጎልብተን ስንገኝ ነው ብለዋል።

በጥንቃቄ በማቀድ፣ በመተግበርና በማዝለቅ በዝግጅት ወቅት የማድረግ አቅማችንን የሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገልፀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በዐውደ-ግንባሩ የሚገኙ ዕዞችን በመወከል አጭር የሥራ ሪፖርት ያቀረቡት ሌተናል ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ ናቸው።

ሠራዊታችን ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህንን ታላቅ በዓል ሲያከብር የህዝባችንና የሠራዊታችንን አብሮነት የበለጠ ያረጋግጣል። የገጠሙንን ፈተናዎች በተባበረ ክንዳችን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለመሻገር ከማስቻሉም በላይ ሀገራችንን በደምና በአጥንት ጠብቀው ያስረከቡን አባቶቻችን ቃል ኪዳን በማጠናከር የምንወዳት ሀገራችን ሠላም ሆና እንድትቀጥል አብሮነታችንን የበለጠ ለማጠናከር በማሰብ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ሌ/ጀኔራል ሰለሞን ኢተፋ አክለውም በግንባሩ ያሉት የጦር ክፍሎች የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ የማድረግ አቅማቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የዝግጅት ሥራዎችን ለወራት ያህል ሌት ተቀን ሲሰሩ እንደነበረም ጠቁመዋል።

በግንባሩ ተሰማርተው የሚገኙ ሁሉም ዕዞች እያንዳንዷ ደቂቃ ሳትባክን በመጠቀም ተደማሪና ተጨማሪ ግላዊ፣ ቡድናዊና አህዳዊ ክህሎትን፣ ወታደራዊ ዕውቀትን እና ጠንካራ አስተሳሰብን በመቅረፅ በየደረጃው የተሰራበት ስለመሆኑም በሪፖርታቸው ተገልጿል።

ብርሃኑ ወርቁ
ፎቶግራፍ ብርሃኑ ወርቁ

ለተጨማሪ መረጃዎች ከታች ያሉትን ሊንኮች ይጠቀሙ። ቴሌግራም 👇

https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0 ፌስቡክ 👇

Exit mobile version