Site icon ETHIO12.COM

«…የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል»

“በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በውስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ዉጥን በፍፁም አይሳካም!”
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በዉስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ዉጥን በፍፁም አይሳካም!” ሲል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል ሶላት በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ በሰላም ተጠናቋል፡፡ አብዛኛዉ ሰላም ወዳድ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረጉት ተሳትፎና ከፀጥታ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ ነዉ፡፡

ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማተራመስና ለማፍረስ እንደ መሳሪያ ከሚጠቀሙባቸዉ ጉዳዮች ዉስጥ የለዉጥ ሂደቱ ፈተና ሆነዉ የቀጠሉት የሃይማኖት ፅንፈኝነት፣ አክራሪነትና መንደርተኝነት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የዉስጥ ባንዳዎች በሃይማኖት ሽፋን ከውጭ ኃይሎችና ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ተቀናጅተዉ ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ለመበጣጠስ፤ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ለማድረግ እንዲሁም ከአንድነት ይልቅ መበታተንና መከፋፈል እንዲፈጠር አልመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በተለይም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ካጋጠመዉ ረብሻ ጋር ተያይዞ ግጭቱን ወደ ደቡብ ክልል ወራቤ ከተማና ወደ ሌሎች አካበቢዎች በማስፋፋት ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሙከራ ማድረጋቸዉ የሚታወስ ነዉ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰሞኑን የፀረ-ኢትዮጵያ አቋሞቻቸዉን በመግለፅ ቀጣይ ሊፈጥሩት ስላሰቡት ሁከት በአደባባይ ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡

ይህንኑ እኩይ ዓለማቸዉን በዛሬም በአዲስ አበባ የታላቁ ዒድ ሶላት ላይ ለመተግበር ሙከራ አድርገዋል፡፡ በሰማዕታት ሃዉልትና በመስቀል አደባባይ በንብረት እና በፀጥታ ሃይሎች ላይ ከደረሰዉ መለስተኛ ጉዳት ዉጭ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ወዳድ አማኞችና በፀጥታ ሃይሎች ቅንጅት የትርምስ ፍላጎቱና ዕቅዱ ከሽፏል፡፡

በቀሪዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የ1443ኛው የታላቁ የኢድ አልፈጥር በዓል ሶላት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዶ በሰላም ተጠናቋል፡፡

መላው ህዝባችን የታሪካዊ ጠላቶቻችና በዉስጣችን የሚገኙ የተላለኪዎቻቸዉን እኩይ ሴራዎች ተገንዝቦ ፅንፈኝነትንና መገፋፋትን በቁርጠኝነት በመታገል ህብረ ብሄራዊ አንድነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ መንግስት በፅንፈኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በየትኛዉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማወቅም ይሁን ባለመወቅ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን አካላት አንድ በአንድ በመልቀም መንግስት የጀመረዉን ህግና ስርዓት የማስከበር ብሎም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህንን ተግባር ለማፈፀም መንግስት ሙሉ ቁርጠኝነትና ጠንካራ አቅም እንደላዉ በዚህ አጋጠሚ ማረጋገጥ እንወደለን፡፡

ዘመን የማይሽረውን የህዝባችንን አንድነትና መተባበር በማጎልበት ሁለም ሰው ያለ ልዩነት ሃይማኖትን፣ ብሄርንና መንደርተኝነትን ማእከል ያደረገዉን አክራሪነትና ፅንፈኝነትን የመወጋት ዘመቻን በፅናት መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራና በዉስጣዊ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እኩይ ዉጥን መቼም ቢሆን አይሰካም!

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የዒድ አልፈጥር በአል እንዲሆን እንመኛለን!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version