Site icon ETHIO12.COM

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕወሓት የፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ለማሳተም ዝግጅት እያደረገ ነው

አሸባሪው ሕወሓት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንዲደርስ የጥናት ውጤቱን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ለማሳተም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና መምህር፣ ተመራማሪና የጥናት ቡድኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረጋቸውን የጥናት ግኝቶች ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጠቃሚ በመሆናቸው በተለያዩ ጆርናሎች ላይ የማሳተም ልምድ አለው። አሸባሪው ሕወሓት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ በተለይ የእንግሊዝኛ አንባቢዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህ የዩኒቨርሲቲው መደበኛ ሥራ በመሆኑ የሚወጡ ጥናቶች በእንግሊዝኛ ይታተማሉ ብለዋል። 

ቡድኑ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው ሴሚናር ለማዘጋጀት ዩኒቨርሲቲው እቅድ አለው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ፤ አውደ ጥናቱ በእንግሊዝኛ የሚቀርብ ይሆናል። ኤምባሲዎችና ማንኛውም ማኅበረሰብ መሳተፍ ይችላል። ይፋ የሆነው የጥናት ውጤት በመሆኑ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይዘት የለውም። ማንም ሰው መጥቶ መታደም ይችላል። ምን ያክል ሰው ጅምላ መቃብር ውስጥ አለ፣ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር የሚለውን ለመለየት ወደ ፊት የፎረንሲክ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በቀጣይ ምርምር ማድረግ የሚጠይቁ ሥራዎች ስላሉ የትኛውም የዓለም አቀፍ ተቋም ለመሥራት ፍላጎት ካለው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፈቃደኛ ነው ብለዋል። 

በጥናቱ ዙሪያ ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተጀመሩ ሥራዎች አሉ ያሉት የቡድን መሪው፤ ከዓለም አቀፍ ምሁራን ጋር ጉዳዩን በጋራ መሥራት የሚችሉ ግለሰቦችና ተቋማት ጋር መነጋገር መጀመሩን ገልጸዋል። 

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ ገለጻ፤ ይህ ጉዳይ በአንድ ሳምንትና ወር የሚፈጸም ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ነው። ጥናቱ የጥናት መርሆችን ተከትሎ የተካሄደና ሙሉ መረጃዎች በእጃችን ያለ በመሆኑ ማየት ይቻላል፤ ነገር ግን የጥናቱን ውጤት ላለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆነ ግለሰብ ካለ አላማው ሌላ ስለሆነ በየትኛውም ቋንቋ ቢቀርብለት ላይቀበል ይችላል። 

እውነትን የሚቀበል ማኅበረሰብ በመረጃ የተደገፈ እውነታዎችን በማውጣት ለማሳየት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። 

ጉዳዩ ከዩኒቨርሲቲው በላይ ስለሆነ የመንግሥት፣ የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት ጭምር መሥራት አለባቸው። የፖለቲካ አላማ ያለው ግለሰብና ተቋም ጥናቱን በማጣጣል ውዥንብር ሊፈጥር ይሞክራል፤ ነገር ግን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አላማ ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ሲል እውነታን የማውጣት ሥራ እየሠራ ነው። 

ጥናቱ እንደሚያሳየው የሰብአዊ መብት፣ የዓለም አቀፍ ወንጀልና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተረሸኑበት ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት፣ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማወቅ ስለነበረበት የጥናቱ ግኝት በፍጥነት ይፋ ሆነ እንጂ ሥራው አለማለቁን ገልጸዋል።

ሞገስ ጸጋዬ via EPA

Exit mobile version