Site icon ETHIO12.COM

ኀላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ከጎንደር የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ኀላፊነታቸውን ያልተወጡ ስድስት የፖለቲካ እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በየደረጃው ከሕዝቡ፣ ከፖለቲካ አመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት እና ግምገማ ከተካሄደ በኋላ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም ተገልጿል።

በጎንደር ከተከሰተው የፀጥታ ችግር በተያያዘ ኀላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ ስድስት የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በየደረጃው ከሕዝቡ፣ ከፖለቲካ አመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት እና ግምገማ ከተካሄደ በኋላ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።

ሰሞኑን በጎንደር ከተማ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተቀስቅሶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

በጎንደር ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደገለጹት፣ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በመፈቃቀር እና በአንድነት ላይ የተመሠረተ አብሮ የመኖር ባህል ያዳበሩ፣ ጠላትን በጋራ ሲመክቱ የቆዩ ናቸው።

በኹለቱ እምነት ተከታዮች መካከል ለዘመናት ተፋቅሮ፣ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር እሴት ለማጠልሸት በውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት የታገዘ የፀጥታ ችግር እንዲነሣ መደረጉን ገልፀዋል።

በችግሩ ምንጭ ዙሪያ፣ ችግሩ በተፈጠረ ጊዜ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በነበራቸው ሚና ዙሪያ መምክሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።

እስካኹን ኀላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ ስድስት የፓለቲካ እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መኾኑን አስታውቀዋል።

በየደረጃው ከሕዝቡ፣ ከፖለቲካ አመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት እና ግምገማ ከተካሔደ በኋላ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ የውጭ ኀይሎች ጣልቃ-ገብነት የተስተዋለ፣ የፀጥታ መዋቅሩ ሥራዎች መላላት፣ የቀበሌ መታወቂያ አሰጣጥ ሥርዐት ክፍተት መኖሩ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አደረጃጀት አለመጠናከር፣ የጦር የመሣሪያ አያያዝ ሥርዐት ችግሮች መኖሩ፣ አወዛጋቢ የቤተ-እምነት ቦታዎች ይዞታ ላይ አፋጣኝ ውሳኔ አለመሰጠቱ ዋና ዋና ችግሮች መኾናቸውን ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች፥ ግጭቱ ጠላቶች ከተማችንን ለማጥፋት የሸረቡት ሴራ ነው፤ ስለዚህ ሕዝቡ አንድነቱን እና የቆየ አብሮነቱን ሊፈታተኑ ከሚችሉ ጠላቶቹ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

“ጎንደርን ስናፈርስ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን” ብለው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኀይሎች በሃይማኖት ሽፋን አንድነታችንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ ፥ እነዚህን አፍራሽ ኀይሎች በተጠናከረ የደኅንነት ሥራ እና በሕዝብ ተሳትፎ ማጋለጥ እና ለሕግ ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸውን አካላትን በሕዝብ ተሳትፎ ማጋለጥ እና ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው በኹለቱ ሃይማኖቶች ሽፋን የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና አመራሩ ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ገልፀዋል።

የመተሳሰብ፣ አንድነት እና ተከባብሮ የመኖር እሴታችንን በመጠበቅ በከተማችን የተጀመረውን ልማት መደገፍ ይገባናል ሲሉም አቶ ዘውዱ ማሳሰባቸውን ከጎንደር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘ መረጃ ያመላክታል። Via . (አሚኮ)

Exit mobile version