ETHIO12.COM

64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወርቅ በቁጥጥር ስር ዋለ

64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ደብቆ ኬላ ጥሶ ለማለፍ የሞከረው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

64 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ደብቆ ኬላ ጥሶ ለማለፍ የሞከረው አሽከርካሪ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፤ የጉምሩክ እና በአካባቢው በነበሩ የኦሮሚያ ክልል የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ11:30 በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ቦረና ከተማ ዶሎ በር ኬላ ሰሌደ ቁጥሩ ኮድ-3-ኢት AA 03775 የሆነ ትዮታ ደብል ፒክአፕ ላንድ ክሩዘር ከነጋሌ ከተማ ወደ ሶማሌ ክልል ለመሄድ ቀጥታ በጉምሩክ ኬላ በኩል መጥቶ ለፍተሻ ሲያስቆሙት ፊቃደኛ ባለመሆን በኬላው ጎን ባለው የእግረኛ መንገድ በመጠቀም ጥሶ ለማለፍ ሲሞክር ለማስቆም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ጥይት ቢተኩሱም ሳይቆም በማምለጥ ላይ እያለ የጉምሩክና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ለነበረው ኮማንድ ፖስት መረጃውን በፍጥነት ማስተላለፉን ገልጿል፡፡

በዚህም ዶሎ በር አካባቢ በሚገኘው የእርዳታ እህል ማራገፊያ አየር ማረፊያ አካባቢ የኦሮሚያ የሚሊሻ ኃይል ባደረጉት ብርቱ ክትትል ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲፈተሽ 16 ኪ.ግ ወርቅ የተገኘ ሲሆን አሁን በገበያ ላይ ባለው ዋጋ በብር ሲተመን 64,000,000.00 ብር (ስልሳ አራት ሚሊዮን ብር) የሚያወጣ መሆኑ ተረጋግጧል።

ከነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅም በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ ከተማ በሚገኘው የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ መጋዘን ገቢ እንደተደረገ ታውቋል::

ምንጭ፡- ፌደራል ፖሊስ

Exit mobile version