Site icon ETHIO12.COM

መንግስት “በመላው አገሪቱ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰድኩ ነው”- የትህነግ ሰርጎ ገቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሃገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሄ የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው!

መላው ህዝባችን ይህንን እኩይ ሴራ በመገንዘብ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ይጠይቃል፡፡ ለሃሰተኛ መረጃዎችና የጥፋት መልእክትን ለያዙ ወሬዎች ጆሮ ባለመስጠት የህግ የበላይነትን የማስከበሩን እርምጃ እንደ እስካሁኑ በሙሉ አቅሙ ማገዙን እንዲቀጥልም ጥሪውን ያቀርባል። መንግስት በበኩሉ በህገወጥ ተግባር ላይ በመሳተፍ፤ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሆነ ብለው፤ አቅደዉ በሚሰሩ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም የሚዲያና የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መንግስት በሕዝብ ጥያቄ መሰረት፣ ህዝብ በተደጋጋሚ የሰላም ያልህና የህግ ይከበር ጥያቄ ሲያሰማ መቆየቱን አስታውሶ በመላው አገሪቱ የህግ ማስከበር ዘመቻ ኦፕሬሽን ላይ መሆኑንን አስታወቀ። “የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲል መግለጫ አወጣ። ሙሉ መግለጫውን ከስር ያንብቡ።

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየውን ህገወጥነትና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም ስርዓት አልበኝነትን መንግስት እንዲቆጣጠር መላ ህዝባችን በተደጋጋሚ በአንድ ድምፅ ሊባል በሚችል መልኩ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ቀደም ሲል ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት እነዚህን ጉዳዮች በመገምገም አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ማስታወቁም የሚታወስ ነው፡፡ ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ የዚሁ አካል ነው፡፡

በኦሮሚያና በአጎራባች ክልሎች የሸኔ የሽብር ቡድን ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር በመተባበር ህዝባችን ላይ እያደረሰ የነበረውን ጥቃት ለመቀልበስ መንግስት የተሳካ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በአልሸባብ የሽብር ኃይል ላይ እየተወሰደ የሚገኘውም እርምጃ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ በአማራ ክልል በህገወጥ የጦር መሳሪያና ገንዘብ ዝውውር፤ በቡድን ተደራጅቶ ግለሰቦች ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ላይ የተሰማሩ፤ በነፍስ ግድያ የሚጠረጠሩ፣ አንዱን ህዝብ ከሌላው ጋር በማጋጨት ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባና በዙሪያው ኦሮሚያ ከተሞች በቡድን ተደራጅተው በልዩ ልዩ የዝርፊያ ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር አቀባባይ በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች፤ እንዲሁም በወያኔ ሰርጎ ገቦች ላይም መንግስት ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡

በሁሉም ክልሎች እየተካሄደ በሚገኘው ኦፕሬሽን በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ከነ ትጥቆቻቸዉ፤ ከዘረፉት ንብረትና ቀጣይ ሊፈፅሙ ያቀዷቸዉ ጥፋቶችን ካሰፈሩባቸው ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ እየተደረገ ነው። ጉዳያቸውም ተገቢውን ሂደት ጠብቆ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡

መንግስት ህግና ስርዓትን በማስከበር የዜጎች ደህንነትና የሀገር ቀጣይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ላለው እርምጃ መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በሁሉም ክልሎች መላው ህዝባችን የጥፋት ሰንሰለቶቹን ከማጋለጥ ጀምሮ አጀንዳውን የሁከትና ብጥብጥ ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎችን እየታገለ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት የመንግስትን እርምጃ ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውን መንግስት አረጋግጧል፡፡

አሸባሪው ህወሃት እና ጀሌዎቹ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ቡድኖችን በተለይም በአማራ ክልል የህግ የማስከበር ስራዎችን ለማደናቀፍ የሚሞከሩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማባባስ ከወዲሁ አጋርነታቸውን በይፋ እየገለፁ ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተን እነዚህ ቡድኖች በተለይም በፋኖ ስም የሚነግዱ የዝርፊያ ቡድኖች በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ክህደት የፈፀሙ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እና የተላላኪዎቻቸው ዓላማ ማስፈፀሚያ መሆናቸው ነው፡፡

መላው ህዝባችን ይህንን እኩይ ሴራ በመገንዘብ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ይጠይቃል፡፡ ለሃሰተኛ መረጃዎችና የጥፋት መልእክትን ለያዙ ወሬዎች ጆሮ ባለመስጠት የህግ የበላይነትን የማስከበሩን እርምጃ እንደ እስካሁኑ በሙሉ አቅሙ ማገዙን እንዲቀጥልም ጥሪውን ያቀርባል። መንግስት በበኩሉ በህገወጥ ተግባር ላይ በመሳተፍ፤ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ሆነ ብለው፤ አቅደዉ በሚሰሩ አካላትና ግለሰቦች እንዲሁም የሚዲያና የጋዜጠኝነት ካባ ደርበው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የዜጎች ሰላም፣ ደህንነትና የሀገር ቀጣይነት የሚረጋገጠው የህግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጰያ የሚገኘው ዜጋ በሰላም ወጥቶ የመገባት መብቱ እንዲከበርና ደህንነቱ እንዲጠበቅ የህግ የበላይነትን ማስፈን ደግሞ ህዝብ ለመንግስት የሰጠው ሃላፊነት ነው።

የዜጎች ነፃነትና ዲሞክራሲም መስፈን የሚችለዉ የትኛዉም ጉልበት አለኝ የሚል አካል ከህግ በታች መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ብቻ ነዉ፡፡ ነፃነትንና መብትን ከለላ በማድረግ የሚፈፀም የትኛውም አይነት እኩይ ተግባርን መንግስት አይታገስም፡፡

መንግስት በሆደ ሰፊነት በተደጋጋሚ ጊዜ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከቁብ ያልቆጠሩ ኃይሎችን መግታት የሚቻለው የህግ የበላይትን በማስከበር ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋና የተለየ አመለካከት ያላቸዉ ወገኖችም መብትና ጥቅሞቻቸዉን ማስከበር የሚችሉት የህግ የበላይነት ሲረጋገጥና ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነዉ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!!

Exit mobile version